በትምህርት ቁሳቁስ እና በምግብ እጥረት ምክንያት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ መራቅ የለባቸውም።

19
ደሴ: ነሐሴ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ከተለያዩ አካላት በማሰባሰብ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የትምህርት ቁሳቁስ ለተማሪዎች ድጋፍ አድርጓል።
በድጋፍ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ በከተማዋ “በትምህርት ቁሳቁስ እና በምግብ እጥረት ምክንያት ትምህርት የማያገኝ ተማሪ መኖር የለበትም” በሚል ተነሳሽነት ከተማ አሥተዳደሩ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል ። ከተደረገው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በተጨማሪ የትምህርት ቤት ምገባ መርሐ ግብር ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት አቶ ሳሙኤል በ2018 የትምህርት ዘመን ከ23 ሺህ በላይ ተማሪዎችን የምገባ መርሐ ግብር ተጠቃሚ ለማድረግ እንደታቀደም ጠቁመዋል።
በትምህርት ቁሳቁስ ማሰባሰብ መርሐ ግብሩ ላይ ድጋፍ ላደረጉ ሁሉ ከተማ አሥተዳደሩ ያመሰግናል ነው ያሉት። የደሴ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ፍቅር አበበ በዕለቱ ከሁሉም የደሴ ከተማ ለተመረጡ 5 ሺህ ተማሪዎች የደብተር፣ የብዕር እና ቦርሳ ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል። ይህ የመጀመሪያ ዙር ድጋፍ ነው ያሉት አቶ ፍቅር በአጠቃላይ ለ20 ሺህ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
የትምህርት ቁሳቁስ የማሰባሰብ ተግባር እንደተጀመረ የግል እና የመንግሥት ተቋማት፣ ባለ ሀብቶች እና በጎ አድራጊ ግለሰቦች ድጋፍ በማድረግ ተሳትፈዋል ብለዋል። የተደረገው ድጋፍ በአጠቃላይ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ እንደተደረገበትም ገልጸዋል።የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገላቸው ተማሪዎች እና የተማሪ ወላጆች የትምህርት ቁሳቁስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወደደ በመምጣቱ ለማሟላት እንደሚቸገሩ ገልጸዋል።ለተደረገላቸው ድጋፍም አመስግነዋል ።
ዘጋባ፦ ከድር አሊ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበአማራ ክልል የተከሰተውን የኮሌራ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር እየተሠራ ነው።
Next articleእየተጠበቀ ያለው የትራምፕ እና የፑቲን ምክክር