
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ)
በክረምት ወቅት በስፋት ከሚከሰቱ ተላላፊ በሽታዎች መካከል የኮሌራ በሽታ ተጠቃሽ ነው። በተለይ በዚህ ወቅት በአማራ ክልል ክስተቱ ስለመስፋፋቱ የክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል።በኢንስቲትዩቱ የበሽታዎች እና የጤና ሁኔታዎች ምላሽ አሰጣጥ ባለሙያ ሲስተር ሰፊ ደርብ እንደሚሉት የኮሌራ ወረርሽኝ ላለፉት ስድስት ወራት በክልሉ ተከስቷል ብለዋል።
ከባለፈው ጥር 2017 ጀምሮ ክስተቱ ማጋጠሙን የተናገሩት ሲስተር ሰፊ አሁን ላይ በክልሉ 42 ወረዳዎች ላይ ስለመከሰቱ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ክስተቱን ተከትሎ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ጥረት በመደረግ ላይ መኾኑንም ተናግረዋል።በክረምት ወቅት የወረርሽኙ የስርጭት አድማስ ይሰፋል ያሉት ባለሙያዋ ይህንን ለመግታት በትኩረት እየተሠራ ስለመኾኑ አስረድተዋል።ሰሜን ጎጃም ዞን፣ ምዕራብ ጎንደር ዞን እና ዋግኸምራ ብሄረሰብ አሥተዳደር ወረርሽኙ በስፋት የተከሰተባቸው ዞኖች ናቸው ብለዋል። ምዕራብ ጎጃም ዞንም በተለያዩ ወረዳዎች የኮሌራ ወረርሽኝ ስለመከሰቱ ተናግረዋል።
ሲስተር ሰፊ ወረርሽኙን በዘለቄታው ለመቆጣጠር እና ለማጥፋት እየተሠራ ነው ብለዋል። የክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የባለሙያዎች ቡድን በማዋቀር ለድጋፍ ወደ ዋግኸምራ ስለመላኩም ተናግረዋል። የአካባቢ ንጽህና ጉድለት ለወረርሽኙ ያጋልጣል ያሉት ሲስተር ሰፊ ከአጋር ተቋማት ጋር በመኾን በሃይማኖት ተቋማት እና ሰው በብዛት በሚሠባሠብባቸው ቦታዎች መፀዳጃ ቤቶችን የመገንባት ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።
የንጹህ መጠጥ ውኃ ችግርን ለመቅረፍም በተመሳሳይ ሥራዎች እየተሠሩ ስለመኾናቸው ለአሚኮ ተናግረዋል።የኮሌራ በሽታ አጣዳፊ የኾነ ተቅማጥ እና ትውከት ምልክቶቹ ሲኾኑ በአፋጣኝ ሕክምና ማግኘት ካልተቻለ ለህልፈት ይዳርጋል።ከግል ንጽህና አጠባበቅ ጀምሮ ምግብን አብስሎ በትኩሱ መመገብ እንደሚገባ ባለሙያዋ መክረዋል።ችግሩ ሲያጋጥም ደግሞ በፍጥነት ወደ ሕክምና ማዕከል መሄድ እና አስታማሚዎችም ጥንቃቄ የተሞላበት እንክብካቤ እንዲያደርጉ ኢንስቲትዩቱ መልዕክቱን አስተላልፏል።
ዘጋቢ፦ ኤልያስ ፈጠነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!