“የ2018 በጀት ዓመት ታላላቅ ሀገራዊ እና ክልላዊ ተልዕኮዎችን የምንፈጽምበት ዓመት ይኾናል” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ

15
ባሕር ዳር: ነሐሴ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት መሪዎች እና ሠራተኞች በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ እየተወያዩ ነው።
በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ በ2017 በጀት ዓመት በተደረገው ጥረት ስኬታማ ተግባራቶችን አሳክተናል ብለዋል። በክትትል እና ቁጥጥር፣ የመራጭ ተመራጭ መድረኮችን በማስኬድ፣ ፎረሞችን በማጠናከር እና ሕግ ማውጣት ስኬታማ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት።ከ10 በላይ አዋጆች የወጡበት ዓመት እንደነበርም አስታውሰዋል። ያለፈውን በጀት ዓመት ጥንካሬዎች የበለጠ በማስቀጠል እና እጥረቶችን በማረም በ2018 በጀት ዓመት የላቀ አፈጻጸም ለማስመዝገብ መዘጋጀት ይገባል ብለዋል።
በ2018 በጀት ዓመት ታላላቅ ሀገራዊ እና ክልላዊ ተልዕኮዎችን የምንፈጽምበት ዓመት ይኾናል ነው ያሉት። የበጀት ዓመቱ ከመደበኛ ተግባራችን ትይዩ የተሳካ እና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ እንሠራለን ብለዋል።የሕዳሴ ግድባችን መጠናቀቁ ሀገራዊ አንድነትን ከማጎልበት በላይ ተሰሚነትን እና የሀገር ክብርን ያሳድጋል ያሉት አፈጉባኤዋ የግድቡ መመረቅ ፋይዳው ትልቅ እንደኾነም ገልጸዋል።
የቀይ ባሕር ጉዳይ የኢኮኖሚ ጉዳይ ብቻ አይደለም፣ ለ140 ሚሊዮን ሕዝብ የሉዓላዊነት እና የሀገር ክብር ጉዳይም ጭምር ነው ብለዋል።
ለስኬታማነቱ የምናደርገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት። ይሄ የፖለቲካ ጉዳይ አይደለም፤ የዛሬ ብቻ ሳይኾን የነገ ልጆቻችን እጣ ፈንታን የምንወስንበት ጉዳይ ነው ብለዋል።ከአማራ ክልል ምክርቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በአዲሱ በጀት ዓመት የተቋሙን ግብ ለማሳካት፣ ለክልሉ ሰላም እና ሁሉን አቀፍ ልማት መረጋገጥ የተቋሙ ሠራተኞች እና መሪዎች እንዲሠሩ አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ63 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
Next articleበአማራ ክልል የተከሰተውን የኮሌራ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር እየተሠራ ነው።