በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ63 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

13
አዲስ አበባ፡ ነሐሴ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸምን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው አገልግሎቱ ከሀገር አቀፍ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም መጀመር ወዲህ ከፍተኛ ገቢ ማግኘቱን ገልጸዋል።ተቋሙ በበጀት ዓመቱ 63 ነጥብ 12 ቢሊዮን ብር ገቢ መሠብሠብ መቻሉ ነው የተመላከተው።ይህም የኤሌክትሪክ ፍጆታ ፍላጎት በ18 ነጥብ 2 በመቶ ማደጉን ተከትሎ የተገኘ መኾኑ ተገልጿል። ተቋሙ አስተማማኝ የኀይል አቅርቦት ለማቅረብ ያደረገው ጥረት ፍሬያማ ኾኗል ነው ያሉት።
የኤሌክትሪክ አገልግሎት የኀይል ብክነትን ለመቀነስ እና አገልግሎቱን ለማዘመን የተለያዩ ርምጃዎችን መውሰዱን ገልጿል።ከእነዚህም ውስጥ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ 53 ሺህ 714 የቆዩ ቆጣሪዎችን በዘመናዊ ስማርት ቆጣሪዎች መተካቱን ነው የጠቆሙት።የአገልግሎቱ የኀይል መቆራረጥ ችግርን ለመቀነስ እና የዲጂታል አውቶሜሽን ቴክኖሎጂን በመተግበር የኀይል አቅርቦትን ጥራት እና አስተማማኝነት ለማሻሻል ጥረት መደረጉም ተገልጿል።
የጥገናና መልሶ ግንባታ ሥራዎችን በፍጥነት እና በጥራት መሠራቱ የዚህ ጥረት አካል መኾኑ ተመላክቷል።በቀጣይ በዚህም መሠረት በኤሌክትሪክ አገልግሎት የተገኙትን መልካም ውጤቶች በማስቀጠል ያሉትን ክፍተቶች በመሙላት እና የኅብረተሰቡን ቅሬታዎች በመፍታት የደንበኞችን እርካታ ለመጨመር እንደሚሠራ አስታውቀዋል።
ይህም የሀገሪቱን ዕድገት ለማፋጠን እና የሕዝብን ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መኾኑን አስረድተዋል።የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከኅብረተሰቡ ጋር በመመካከር፣ አሠራሮችን በማዘመን እና ተመጣጣኝ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ የገቢ ምንጩን ለማሳደግ እየሠራ መኾኑም በመግለጫው ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አሰፌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) መልዕክት፦
Next article“የ2018 በጀት ዓመት ታላላቅ ሀገራዊ እና ክልላዊ ተልዕኮዎችን የምንፈጽምበት ዓመት ይኾናል” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ