ለትምህርት የደረሱ ሕፃናት ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ እና ትምህርታቸውን ያቋረጡም እንዲመለሱ ጥሪ ቀረበ።

24
ደብረብርሃን፡ ነሐሴ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ሸዋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኤልያስ አበበ ሰሜን ሽዋ ትምህርት እና ጥበብን መገለጫው ያደረገ ሕዝብ የሚኖርበት አካባቢ ነው ብለዋል።የሰሜን ሸዋ ሕዝብ ለትምህርት ባለው የቆየ ግንዛቤ ከ22 በላይ መጻሕፍትን የጻፉት የአጼ ዘርዓ ያዕቆብ፣ የአጼ ዳዊት እና የዘመናዊ ትምህርት ጀማሪው የአጼ ምኒሊክን ጨምሮ የበርካታ ደራሲያን ፣ ምሁራን፣ ፈላስፎች እና ዲፕሎማቶች መፍለቂያ እንደኾነም ጠቁመዋል። ይህ ታሪክ ዛሬም በሰሜን ሸዋ ቀጥሏል ብለዋል።
አሁን ላይ ግን በሰላም እጦት ምክንያት ከትምህርት ገበታ የወጡ ተማሪዎች ቁጥር ቀላል የማይባል በመኾኑ ድርጊቱ የሸዋን ሕዝብ ማንነት የማይመጥን ነው ብለዋል። የልጆች ከትምህርት መራቅ የሁሉም ቁጭት መኾን አለበት ነው ያሉት።”እንደ አባቶቻችን ነገ ባለ ታሪክ መኾን ከፈለግን ትምህርትን ከሁሉም ሥራዎቻችን ቀዳሚ በማድረግ በባለቤትነት መያዝ እና በተገቢው መንገድ መደገፍ አለብን” ብለዋል።
ትምህርት ከፖለቲካዊ እሳቤ በላይ መኾኑን የገለጹት ኀላፊው የሕዝብ ጥቅምን አስጠብቃለሁ የሚል ማንኛውም ኀይል በትምህርት፣ በትምህርት ተቋማት ደኅንነት እና በነገው ትውልድ ግንባታ ላይ መደራደር እንደሌለበት ተናግረዋል።በ2018 የትምህርት ዘመን ሁሉም ለትምህርት የደረሱ ሕፃናት ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ እና ትምህርታቸውን ያቋረጡም እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።የዞኑ የ2018 የትምህርት ዘመን በታቀደለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንዲጀመር እና ስኬታማ እንዲኾን ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበጦርነቱ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት እየተሠራ ነው።
Next articleየጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) መልዕክት፦