
ሰቆጣ፡ ነሐሴ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ በማቋቋም የሚታወቀው ዩ ኤን ዲ ፒ ፒስ ሳፖርት ፋሲሊቲ የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት በአብርገሌ ወረዳ ወጣቶች የሥራ ፈጠራ እና የኑሮ መሻሻል ላይ ትልቅ ለውጥ ማምጣቱን ወጣቶቹ ገልጸዋል።
ወይዘሮ አያልነሽ ዘሪሁን በአብርገሌ ወረዳ ኒየረአቑ ከተማ ነዋሪ ሲኾኑ ቀደም ሲል በመንግሥት መስሪያ ቤት ጸሐፊነት ይሠሩ እንደነበር ይናገራሉ።በጦርነቱ ምክንያት ሥራቸውን በማቋረጥ ወደ አዲስ አበባ በመሄድ የቤት እቃዎች (ፈርኒቸር) ሥራ ሥልጠና ወስደዋል። ሥራውን ለመጀመር በሚያስቡበት ጊዜም በዩ ኤን ዲ ፒ ፒስ ሳፖርት ፋሲሊቲ ከተሰጣቸው የ21 ሺህ ብር ድጋፍ በተጨማሪ ከባንክ ብድር 200 ሺህ ብር በማግኘት የራሳቸውን ንግድ መጀመር ችለዋል።
አሁን ላይም ለሦስት ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን እና ብድራቸውን ከፍለው የራሳቸውን ገቢ ማሳደግ እንደቻሉ ገልጸዋል። የአብርገሌ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ነይኑ በላይ በበኩላቸው የዩ ኤን ዲ ፒ ፒስ ሳፖርት ፋሲሊቲ ከ2015 ዓ.ም እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ በትምህርት ተቋማት፣ በጤና ጣቢያዎች እና በንጹህ መጠጥ ውኃ መሠረተ ልማቶች ላይ የድጋፍ ሥራ ማከናወኑን አብራርተዋል። ድርጅቱ በአጠቃላይ ከ77 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ በማድረግ በወረዳው በጦርነቱ የወደሙ ተቋማትን እንደገና ለመገንባት መቻሉን ገልጸው ለተደረገው ድጋፍም ምሥጋና አቅርበዋል።
የአማራ ክልል የመልሶ ማቋቋም ፈንድ ጽሕፈት ቤት የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ክላስተር ቡድን መሪ መለሰ ተፈራ (ዶ.ር) በበኩላቸው ዩ ኤን ዲ ፒ ፒስ ሳፖርት ፋሲሊቲ በአማራ ክልል በሚገኙ ስምንት ወረዳዎች ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል። ይህ ድጋፍ ከተቋማት ግንባታ በተጨማሪ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከፍ በማድረግ በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳደረገም ነው የተናገሩት።
በኢትዮጵያ ዩ ኤን ዲ ፒ ፒስ ሳፖርት ፋሲሊቲ ዋና ዳይሬክተር ሞንሴፍ ካርተስ (ዶ.ር) በአብርገሌ ወረዳ የተሠሩ ልማቶችን እና ተቋማትን ከጎበኙ በኋላ እንደተናገሩት ድርጅቱ ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ የሚሠራ ነው ብለዋል። ጦርነት የመሠረተ ልማቶች ጸር መኾኑን በመጥቀስ ባለፉት ዓመታት በጦርነቱ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት ከኢትዮጵያ እና ከክልሉ መንግሥት ጋር በመተባበር ሢሠሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል። የተገኘው ውጤት የድርጅቱ ሳይኾን የመንግሥት እና የሕዝቡ ጥረት ውጤት መኾኑንም አብራርተዋል።
በቀጣይም የተጀመሩ የመልሶ ማቋቋም ድጋፎችን ማጠናከር ላይ እንደሚሠሩ እና ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በጉብኝቱ ዩ ኤን ዲ ፒ ፒስ ሳፖርት ፋሲሊቲ ግብረሰናይ ድርጅት ከፍተኛ መሪዎች፣ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ እና የአብርገሌ ወረዳ የሥራ ኀላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!