ምክንያቱ ያልታወቀ የአንጀት ቁስለት ምንድን ነው?

54
ባሕር ዳር: ነሐሴ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በፈለገ ሕይዎት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ሐኪም ዶክተር ማናለ ጥላሁን አንጀት ከጉሮሮ የመዋጫ ቱቦ ጀምሮ ያለውን የአንጀት ክፍል ማለትም የምግብ ቱቦ (ጉሮሮ)፣ ጨጓራ፣ ቀጭን አንጀት እና ወፍራም እንጀትን የሚያካትት ነው ይላሉ።
ዶክተር ማናለ እንዳሉት አንጀት የመጀመሪያ ግድግዳ፣ የጡንቻ እና የውጭ ሽፋን ግድግዳ ክፍሎች አሉት። እነዚህ ክፍሎች ላይ መቆጣት፣ ማበጥ ወይም መቁሰል ሲያጋጥም የአንጀት ቁስለት ተብሎ ይጠራል ብለዋል። ለዛሬ ግን “ኢንፍላማቶሪ ባውል ዲዝዝ” (IBD) ወይም ምክንያቱ ያልታወቀ የአንጀት ቁስለት እየተባለ ከሚጠራው የአንጀት ቁስለት ላይ ትኩረት አድርገናል።
እንፍላማቶሪ ባውል ዲዝዝ ወይም ምክንያቱ ያልታወቀ የአንጀት ቁስለት እየተባለ የሚጠራው የመጀመሪውን የቀጭን አንጀት ክፍል እና ጨጓራን የሚያጠቃው ዓይነት ነው። ከዚህ በፊት በአደጉ ሀገራት ከ100 ሰዎች ውስጥ 30 የሚኾኑት በዚህ በሽታ ስለሚጠቁ ያደጉ ሀገራት በሽታ ተደርጎ ይወሰድ ነበር ነው ያሉት።
ይሁን እንጅ አሁን ላይ በአፍሪካ በሽታው እየተስፋፋ መኾኑን ገልጸዋል። እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ ሀገራት ደግሞ ሥርጭቱ እየጨመረ ከሚገኝባቸው ሀገራት ውስጥ ይጠቀሳሉ ብለዋል። በሽታው በአብዛኛው ከ15 እስከ 30 ዓመት ዕድሜ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ያጠቃል። ይሁን እንጅ በሕጻናት እና ዕድሜያቸው በገፉ ሰዎች ላይም አልፎ አልፎ እንደሚከሰት ነው የገለጹት።
በሽታ ከተከሰተ በኋላም የሕክምና ሂደቱ ረጅም ጊዜ መውሰዱ እና ብዙ ምርመራዎችንም የሚጠይቅ መኾኑ፣ ከሚያደርሰው ጉዳት እና ከማኅበረሰቡ ግንዛቤ ማነስ ጋር ተያይዞ አሳሳቢ እየኾነ መምጣቱንም ገልጸዋል።
የበሽታው አጋላጭ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
በሳይንስ የተረጋገጠ ምክንያት ባይኖርም አጋላጭ ምክነያቶች ግን ተቀምጠዋል። የማኅበረሰቡ የአኗኗር ዘይቤ መቀየር አንዱ አጋላጭ ኾኖ ተቀምጧል። ይህ ማለት የአመጋገብ ሥርዓት አንዱ ሲኾን የተጣሩ እና ስብ የበዛባቸው ምግቦች እንደ አጋላጭ ኾነው ተቀምጠዋል።የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መዳከም፣ አልፎ አልፎ ደግሞ የቫይታሚን እጥረት እና ሌሎች ምክንያቶች ናቸው። እንደ ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ሰሊጥ የመሳሰሉ በፋይበር የበለጸጉ ምግቦች ደግሞ በሽታውን የመከላከል አቅማቸው ከፍተኛ መኾኑን ገልጸዋል።
በተደጋጋሚ ለጸረ ተዋህሲያን መድኃኒቶች መጋለጥ በተለይም ደግሞ ለሕመም ማስታገሻነት ተብለው የሚወሰዱ መድኃኒቶች፣ የአልኮል መጠጥ እንድሁም ሲጋራ ማጨስ የማጋለጥ ዕድሉ ከፍተኛ መኾኑን ተናግረዋል።ባልተለመደ ሁኔታ የአንጀት ተህዋሲያን የመከላከል አቅም ባለተፈለገ መጠን መጨመር፣ የዘር ተጋላጭነት፣ በተደጋጋሚ በአንጀት ተህዋሲያን መጠቃት፣ ከፍተኛ ውፍረት፣ ከፍተኛ ጭንቀት እና እንቅልፍ ማጣትም እንደ አጋላጭ ተደርገው ይወሰዳሉ።
የሆድ ሕመም፣ ቁርጠት፣ ተቅማጥ፣ የቆዳ ቁስለት፣ ቁርጥማት፣ ሕመም ያለው የዓይን መቅላት፣ ማስማጥ፣ ከአቅም በላይ የኾነ ድካም፣ የደም ማነስ ምልክቶች፣ የክብደት መቀነስ፣ የሰውነት ሙቀት፣ የምግብ ፍላጎት ማጣት ደግሞ የበሽታው ዋና ዋና ምልክቶች ናቸው።የአንጀት ቁስለትን ለመለየት በምስል የታገዘ የአንጀት ምርመራ (የኢንዶስኮፒ ምርመራ) ዋነኛው እንደኾነ ዶክተር ማናለ ተናግረዋል። አጠራጣሪ ነገሮች ከታዩ ደግሞ እንደ የሥነ ደዌ፣ የላብራቶሪ፣ ሲቲ ስካን፣ ኤም.አር.አይ የመሳሰሉ ተጨማሪ ምርመራዎችም ሊከናወኑ ይችላሉ።
በሽታው ከታወቀ በኋላ የመጀመሪያው ሥራ የተቆጣውን ወይንም የቆሰለውን ክፍል በመድኃኒት መመለስ ወይንም ማስታገስ ነው ብለዋል ዶክተር ማናለ።ሌላኛው ሕክምና ከአንጀት ቁስለቱ ጋር ተያይዞ የመጡ የጎንዮሽ ምልክቶችን በተመሳሳይ ሰዓት የማከም ሥራ ይሠራል ነው ያሉት። የሕክምና ክትትሉን ማስቀጠል ይገባልም ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከወጣቶች ጋር በባሕር ዳር እየመከረ ነው።
Next articleአሚኮ በምሥራቅ ጎጃም ዞን የሚገኙ ቅርሶችን በማስተዋወቅ ረገድ ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡