አልማ ለመቄዶንያ የአረጋዊያን እና የአዕምሮ ሕሙማን ማዕከል የሕክምና መሣሪያዎችን ድጋፍ አደረገ።

9
አዲስ አበባ፡ ነሐሴ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ለመቄዶንያ የአረጋዊያን እና የአዕምሮ ሕሙማን ማዕከል ከ13 ሚሊዮን በላይ ብር የሚያወጡ የተለያዩ የሕክምና መሣሪያዎችን ዛሬ አስረክቧል።
ወደ መቄዶንያ የሚመጡ የተጎዱ እና ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ወገኖች ናቸውም ተብሏል። የተደረገው ድጋፍ ወደ ማዕከሉ የሚመጡ ወገኖችን ጤና ከመጠበቅ ባሻገር በማዕከሉ የተጠለሉ ወገኖችን ሕይዎት የሚያሻሽል መኾኑን ተጠቃሚዎች ተናግረዋል። ድጋፉ በሕክምና መሳሪያዎች እጥረት ይገጥማቸው የነበረውን ችግር በመፍታት በኩል ሚናው የላቀ መኾኑን በመቄዶንያ አረጋዊያን እና አዕምሮ ሕሙማን ማዕከል የሚገኙ አረጋዊያን ገልጸዋል።
የመቄዶንያ ማኅበር መሥራች የክቡር ዶክተር ቢኒያም በለጠ ተወካይ አቶ አሰፋ ባለሄር አልማ ያደረገው የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ የማዕከሉን የዕለት ተዕለት አገልግሎት አሰጣጥ የሚያሻሽል መኾኑን ገልጸዋል። ሌሎችም ማኅበራት እና በጎ አድራጊዎች ለማዕከሉ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል። የአልማ ዋና ሥራ አሥፈፃሚ መላኩ ፈንታ ማኅበሩ ከሮተሪ ወርልድ ኸልፕ ከተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት በአቶ ማርቆስ እና በባለቤታቸው በወይዘሮ እየሩሳሌም አስተባባሪነት ያገኘውን ድጋፍ ማስረከቡን ገልጸዋል።
መቄዶንያን መደገፍ ሀገርን እና ወገንን መደገፍ በመኾኑ ማኅበሩ ድጋፉን ማድረጉን ተናግረዋል። ማኅበሩ በቀጣይም ድጋፍ ለሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። አልማ የዛሬውን ጨምሮ ከዚህ ቀደም የ17 ሚሊዮን ብር አልባሳት እና ሌሎች ድጋፎችን በሦሥት ዙሮች ማድረጉ ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ኢብራሂም ሙሐመድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleከነገ ጀምሮ ምርጫ እንደሚያካሂድ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አስታወቀ።
Next article“ከዕድሜው ያለፈ፤ በብርታቱ የገዘፈ”