
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሙሐመድ ይማም (ዶ.ር) “ምርጫ ለጽኑ ተቋም፤ ምርጫችን በመስጅዳችን” በሚል መሪ መልዕክት የሚደረገውን ምርጫ አስመልክተው በጽሕፈት ቤታቸው መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም የምርጫ አስፈጻሚ ቦርዶች እስከ ወረዳ ድረስ መቋቋማቸውን ተናግረዋል። በምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ በኦንላይን እና በመዝገብ ደረጃ ሲካሄድ ቆይቷል ያሉት ሰብሳቢው ምዝገባው ሐምሌ 30/2017 ዓ.ም መጠናቀቁን አስታውሰዋል። በርካታ ሙስሊሞችም ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ መውሰዳቸውን ተናግረዋል።
ምርጫው በአምስት ደረጃዎች ተከፋፍሎ ነገ ነሐሴ 09/2017 ዓ.ም ዑለማዎችን በመምረጥ ይጀመራል ብለዋል። ቀጣይ ባሉት ቀናት ውስጥም በምሁራን፣ ወጣቶች፣ ሴቶች እና ማኀበራዊ ዘርፍ ምርጫዎች እንደሚካሄዱ ነው የተናገሩት። የዘንድሮው የምርጫ በአሳታፊነቱ፣ በመስጅድ የሚካሄድ በመኾኑ እና በአካታችነቱ ለየት ያለ እንደሚኾን ተስፋ አለን ነው ያሉት። ምርጫው ኀብረ ብሔራዊ እና ሃይማኖታዊ በመኾኑ ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት ሚናው ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ሙስሊሙ ማኀበረሰብ ምርጫችን በመስጅዳችንን ዓይነት አጋጣሚ እንዲያገኝ ለዘመናት ሲጠይቀው ነበር ያሉት ሰብሳቢው ያገኘውን ዕድል በአግባቡ ሊጠቀምበት እንደሚገባም አሳስበዋል። በዑላማ፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ ምሁራን እና ማኀበራውያን ዘርፎች ለሚካሄደው ምርጫ ሕዝበ ሙስሊሙ በንቃት በመሳተፍ በየደረጃው ያሉ መሪዎችን እንዲመርጥም ጥሪ አቅርበዋል። ምርጫው በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ የሰላም እና ጸጥታ አካላት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉም ጠይቀዋል። ዘንድሮ ምርጫ የማይካሄድባቸው አንዳንድ አካባቢዎች በቀጣይ የማሟያ ምርጫ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፦ በሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን