በደሴ ከተማ አሥተዳደር የፖሊስን ሥራ ለማዘመን እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች አበረታች ናቸው።

19
ደሴ: ነሐሴ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በደሴ ከተማ አሥተዳደር በግንባታ ላይ የሚገኘውን የደሴ ከተማ አሥተዳደር የፖሊስ መምሪያ ሕንጻ ግንባታን ተመልክተዋል።
በምልክታ መርሐ ግብሩ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ (ዶ.ር) ጨምሮ ሌሎች የክልል እና የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።፡አዲሱ የደሴ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የቢሮ ሕንፃ ከከተማዋ የተውጣጡ በጎ ፍቃደኛ ባለሀብቶች ነው እየተገነባ የሚገኘው። ከበጎ ፍቃደኛ ባለሀብቶች መካከል አንዱ አህመድ ኢብራሂም እንዳብራሩት ሕንፃው ደረጃውን የጠበቀ እና አስፈላጊ ግብዓቶች የተሟሉለት መኾኑን ገልጸዋል። በቀጣይ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ለማጠናቀቅ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ የደሴ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ሕንፃን ለመሥራት እና የፖሊስን ሥራ ለማዘመን በጎ ፍቃደኞችን በማስተባበር ከተማ አሥተዳደሩ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው ብለዋል። በቀጣይም ከተማ አሥተዳደሩ ተከታታይ እና ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላል ብለዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ (ዶ.ር) የልማት እና የጸጥታ ሥራዎች የማይለያዩ መኾናቸውን ገልጸዋል። ፖሊስን ለማዘመን የሚሠሩ ሥራዎች የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል። በቀጣይ ጊዜያት ፖሊስን ለማዘመን ለሚሠሩ ሥራዎች ድጋፍ ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል። በደሴ ከተማ እየተሠሩ ላሉ ሥራዎችም የከተማ አሥተዳደሩን እና በጎ ፍቃደኛ ነጋዴዎችን አመስግነዋል።
ዘጋቢ:- ደምስ አረጋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleወጣቶች በሰላም እና በልማት ላይ እያደረጉት ያለውን ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀረበ።
Next articleአሚኮ ወንድማማችነት እንዲጎለብት አድርጓል።