
ጎንደር: ነሐሴ 8/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር “ትናንት እና ዛሬን ለዘላቂ ሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ መልዕክት ከልዩ ልዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ የጎንደርን ሰላም እና ጸጥታ በማስከበር የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በከተማዋ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሠረተ ልማቶች መገንባታቸው ተመላክቷል።
በኮሪደር ልማት ለተነሱ ግለሰቦች የቤት መገንቢያ ቦታ ለመስጠት መሠራቱ፤ የገቢያ መሠረተ ልማትን ለማስፋፋት በ160 ሚሊዮን ብር ሸድ መገንባቱ፤ የጎንደር አብያተ መንግሥታት ቅርስ ጥገና እና ሌሎችም በከተማ አሥተዳደሩ በተያዘው በጀት ዓመት ከተሠሩ ሥራዎች መካከል መኾናቸው ተጠቅሷል።
የወጣቶችን የስፖርት ማዘውተሪያ ለማስፋት የፋሲለደስ ስታዲየም እድሳት መጀመሩም ተገልጿል። ወጣቶች ሰላምን በማረጋገጥ ሥራ እና በልማት ተሳታፊ እንዲኾኑ መሠራቱም ተገልጿል።
በ2017 በጀት ዓመት ከ47 ሺህ በላይ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ በቋሚነት ከ30 ሺህ እና በጊዜያዊነት ከ21 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩ ተነስቷል። የሰላም እጦት በሚያሳድረው ጫና ምክንያት በከተማዋ ወጣቶችን ይበልጥ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ እንቅፋት መፍጠሩ ተጠቅሷል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች በወጣቶች ተሳትፎ የታገዙ መኾናቸውን አንስተዋል።
ጎንደር ሀገራዊ ጉባኤዎችን ማካሄድ እንድትችል የከተማው ማኅበረሰብ ሰላምን በማስጠበቅ በኩል መልካም ተግባር መፈጸሙን ገልጸዋል። በዚህም የምጣኔ ሃብቱ በከተማዋ እየተነቃቃ መምጣቱን ተናግረዋል።
ለጎንደር ዕድገት የከተማዋ ወጣቶች ሚና ከፍተኛ በመኾኑ በሰላም እና በልማት ላይ እያደረጉት ያለውን ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።
የጎንደር ልማት ለማኅበረሰቡም ጠቀሜታ ያለው መኾኑን አንስተዋል። ለከተማዋ ሰላም እና ዕድገት ሁሉም በትኩረት ሊሠራ ይገባል ብለዋል። የጎንደር ታሪክ እና ዝና የሚቀጥለው ወጣቶች የአካባቢያቸውን ሰላም ተባብረው ሲያረጋግጡ እንደኾነ ተገልጿል።
በቀጣይ የጎንደርን ታሪካዊነት የሚመጥኑ የልማት ተግባራት እንደሚከናወኑም ተጠቁሟል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋ መኮንን ብልሹ አሠራርን ለማስቀረት፣ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ ልማትን ለማስቀጠል እና የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የአካባቢያቸውን ሰላም ለማስጠበቅ እየሠሩ መኾኑን ጠቁመዋል። በከተማዋ እየተከናወነ ባለው የልማት እንቅስቃሴ ደስተኛ መኾናቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይ ወጣቶችን ይበልጥ በልማቱ ዘርፍ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችም እንዲከናወኑ ጠይቀዋል።
ዘጋቢ :- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!