“ድጋፉ ከኔ አልፎ ደብተር በምን ልግዛላት የሚለውን የእናቴን ጭንቀት ያቀለለ ነው” ድጋፍ የተደረገላት ተማሪ

10

ባሕር ዳር: ነሐሴ 8/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮ ቴሌ ኮም ሰሜን ምዕራብ ሪጅን በባሕር ዳር ከተማ በመስከረም 16 አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የትምህርት ቁሳቁስ ችግር ላለባቸው ተማሪዎች ድጋፍ አድርጓል፡፡

ተማሪ ሄለን በርሄ ዛሬ ኢትዮ ቴሌ ኮም የደብተር ድጋፍ ካደረገላቸው ተማሪዎች መካከል አንዷ ናት፡፡ ተማሪ ሄለን እናቷ አካል ጉዳተኛ በመኾናቸው እና የገቢ ምንጭ እጥረት ስላለባቸው የትምህርት ቁሳቁስ ለማሟላት ትቸገር እንደነበር ገልጻለች። ከጎረቤት በሚማር ልጅ አሮጌ ደብተር ትማር እንደነበርም ተናግራለች፡፡

“ዛሬ ግን ኢትዮ ቴሌ ኮም የአንድ ደርዘን ደብተር ድጋፍ አድርጎልኛል፤ ድጋፉ ከኔ አልፎ ደብተር በምን ልግዛላት የሚለውን የእናቴን ጭንቀት ያቀለለ ነው” ብላለች፡፡ በዚህም ደስተኛ መኾኗን በመግለጽ ረጅ ድርጅቱን አመሥግናለች፡፡ ወደፊት ጠንክራ ተምራ እናቷን ለመደገፍ ጥረት እንደምታደርግም ነግራናለች፡፡

ሌላው ተማሪ ዩሴፍ ዓባይ በቤት ውስጥ ሌሎች ወንድም እና እህቶች እንዳሉት እና አባታቸው ብቻ በሚሠራው ሥራ የሁሉንም የትምህርት ቁሳቁስ መግዛት እንደማይችል ነው የተናገረው፡፡ የተደረገለት ድጋፍ የአባቱን ጫና እንደቀነሰለት ገልጿል። ለተደረገለት ድጋፍም ምሥጋና አቅርቧል፡፡ በቀጣይ ጠንከሮ በመማር አባቱን የመርዳት ዓላማ እንዳለው ነግሮናል፡፡

በባሕር ዳር ከተማ መስከረም 16 አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርእሰ መምህር ብርሃኑ ወርቄ ትምህርት ቤቱ በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ቤተሰብ ያላቸው ተማሪዎችን በመለየት ለማገዝ መሥራቱን ገልጸዋል።

ችግር ያለባቸውን ተማሪዎች ቀድመው በመመዝገብ፣ ፕሮጀክት በመቅረጽ እና እገዛ ማድረግ ለሚፈልጉ ሁሉ ዝርዝሩን በመስጠት በረጅ ድርጅቶች እንዲደገፉ እየተደረገ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡ ትምህርት ቤቱም በራሱ ያቅሙን ያክል ይደግፋል ነው ያሉት፡፡ ይህ ድጋፍ ለተማሪዎች የሚያስፈልጋቸውን ከማሟላት ባለፈ ትልቅ የሥነ ልቦና እገዛ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡

ተማሪዎች ሳይሸማቀቁ እንዲመጡ እና ቋሚ ድጋፍ እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ ይሠራል ብለዋል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ሰሜን ምዕራብ ሪጅን የፋይናንስ እና አሥተዳደር ሥራ አሥኪያጅ ሚሊዮን ጌታ ኢትዮ ቴሌኮም ከሚያገኘው ገቢ በተለያዩ ዘርፎች ድጋፎችን እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ ዛሬም በባሕር ዳር ከተማ በመስከረም 16 አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመገኘት አንድም ተማሪ በትምህርት ቁሳቁስ ምክንያት ትምህርት ማቋረጥ የለበትም በሚል ድጋፍ አድርጓል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም የአንድ ሀገር የኢኮኖሚ መሠረት ትምህርት ነው ብሎ ያምናል ያሉት ሥራ አሥኪያጁ ከዚህ በፊትም በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ለሚገኙ ሴት ተማሪዎች ወርሐዊ የኪስ የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

ለተለያዩ ትምህርት ቤቶች የኢንተርኔት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ሥራ እየሠራ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡ በቅርብ ጊዜ ለተካሄደው የ12ኛ ክፍል የኦን ላይ ፈተና ኔት ወርክ ያለምንም መቆራረጥ እንዲኖር በማድረግ ተማሪዎች ፈተናቸውን በተሳካ ሁኔታ እንዲፈተኑም አድርጓል ነው ያሉ፡፡ ወደፊትም ኢትዮ ቴሌ ኮም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ መኳንንት አደመ የክልሉ የትምህርት ሥርዓት ብዙ ፈተና ገጥሞታል ነው ያሉት።

የ2018 የትምህርት ዘመንን ውጤታማ ለማድረግ ከትምህርት ገበታ ውጭ የኾኑ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ የትምህርት ቁሳቁስን ለማሟላት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ የትምህርት ቁሳቁስን ማሟላት “አንድ ደርዘን ደብተር ለአንድ ተማሪ” በሚል መሪ መልዕክት በንቅናቄ ተጀምሯል ያሉት ምክትል ኀላፊው ይህ ንቅናቄም የትምህርት ሽፋንን ለማሳደግ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ ያሉ የመንግሥት ተቋማት፣ ረጅ ድርጅቶች እና አትራፊ ተቋማት የትምህርት ሥርዓቱን መደገፍ ዋነኛው ተግባራቸው ሊኾን ይገባል ነው ያሉት፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ሰሜን ምዕራብ ሪጅን ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል። በቀጣይም ተቋሙ ይህንን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ዘጋቢ:-ሰናይት በየነ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየበጎ አድራጎት ሥራዎች ባሕል እየኾኑ ነው።  
Next articleወጣቶች በሰላም እና በልማት ላይ እያደረጉት ያለውን ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀረበ።