
ባሕር ዳር: ነሐሴ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት የጤና መድኅን እና ሃብት አሰባሰብ ዕቅድ አፈጻጸም የግምገማ መድረክ እያካሄደ ነው።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ መልካሙ ጌትነት ሃብት የጤና መሠረተ ልማቶች የሚሟሉበት መሠረታዊ ጉዳይ መኾኑን ተናግረዋል። የሃብት ምንጮችን በተገቢው መንገድ በመለየት በሚፈለገው ልክ መሰብሰብ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የሚሰበሰበው ሃብትም ተገቢውን ቁጥጥር በማድረግ ለሚፈለገው ዓላማ መዋሉንም ማረጋገጥ እንደሚገባ አመላክተዋል።
ተግባሩን ቀጣይነት እና ዘላቂነት ባለው መልኩ በማስቀጠል ማኀበረሰቡ ፍትሃዊ አገልግሎት እንዲያገኝ ማስቻል ይገባል ነው ያሉት። የሚሰበሰበው ሃብት እየጨመረ በሄደ ቁጥር የማይበገር የጤና ሥርዓት ለመገንባት እንደሚያስችልም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ክሽን ወልዴ የማኀበረሰብ ዓቀፍ ጤና መድኅን በክልሉ በስፋት እየተተገበረ መኾኑን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ ከ15 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ የቤተሰብ አባላት በጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚ መደረጋቸውን ገልጸዋል። ከባለፉት ዓመታት አፈጻጸም አንጻር የ16 በመቶ እድገት እንዳለውም ነው የገለጹት።
ለጤና መድህን የሚኾን 5 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉንም ነው የተናገሩት። በአገልግሎት አሰጣጡ የሚገጥመውን የመድኃኒት እጥረት ለመቅረፍ በክልሉ ከ52 በላይ የማኅበረሰብ አቀፍ መድኃኒት ቤቶች አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉንም ተናግረዋል።
በመድረኩ ላይ ተሳታፊ የኾኑት የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አሥተባባሪ ፈቃዴ ያለው ጤና መድህን አንድም ሰው በችግር ምክንያት መሞት የለበትም በሚል እሳቤ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል።
እንደ ከተማ አሥተዳደር የጤና መድኅን አገልግሎት ከዓመት ዓመት እያደገ መምጣቱንም አንስተዋል። ማኅበረሰቡ ጥቅሙን በመረዳቱ እየጨመረ መምጣቱን ነው የተናገሩት።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ አንሻ መሐመድ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከ80 በመቶ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀምና ማኅበረሰቡን በማወያየት ውጤታማ የጤና መድኅን ሃብት ማሰባሰብ መቻሉንም ነው የተናገሩት።
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!