የፍትሕ ሥራ አንድ ቦታ ላይ የሚያልቅ አይደለም።

5
ባሕር ዳር: ነሐሴ 8/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት የትብብር ጥምረት የ2017 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም እና የ2018 ዓ.ም የዕቅድ ውይይት መድረክ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ የትብብር ጥምረቱ ባለፈው በጀት ዓመት ያከናወናቸው ዝርዝር ተግባራት ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። ጥምረቱ በክልሉ ሕግ እና ፍትሕ ይሰፍን ዘንድ ከላይ እስከ ታች ድረስ ባሉ መዋቅሮች ግቦችን በማስቀመጥ እና በማለም ሲንቀሳቀስ እንደነበር በሪፖርቱ ተመላክቷል። የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም ለክልሉ የፍትሕ አገልግሎት መሳለጥ የትብብር ጥምረቱ ሚናው ከፋተኛ እንደኾነ ተናግረዋል። ከጊዜ ወደ ጊዜ የፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የሚታየውን ክፍተት ለመፍታትም የትብብር ጥምረቱ ትልቅ ድርሻ እየተወጣ እንዳለ ነው የገለጹት። ወጥ የኾነ ተቋማዊ አደረጃጀትም እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት።
“የፍትሕ ሥራ አንድ ቦታ ላይ የሚያልቅ አይደለም” ያሉት አቶ ብርሃኑ የፍትሕ ጉዳይ ሰንሰለቱን እና አሠራሩን ጠብቆ የሚያልፍ ነው ብለዋል። ለዚህ ውጤታማነትም የፍትሕ እና የሕግ ተቋማት ተባብረው እና ተቀናጅተው መሥራት አለባቸው ነው ያሉት። በዚህ ዘርፍ ባሳለፍነው በጀት ዓመት የትብብር ጥምረቱን ከፊት ኾኖ በመምራት እና በማሳለጥ በኩል የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምሥጋና የሚገባው ነው ብለዋል። የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው የትብብር ጥምረቱ በ2017 በጀት ዓመት በርካታ የፍትሕ ሥራዎች የተከናወኑበት እንደነበር አንስተዋል። ክልሉ የሕግ የበላይነት የሰፈነበት እና ፍትሕ የሰፈነበት እንዲኾን የትብብር ጥምረቱን በቀጣይ አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ነው ያሉት።
ለሕዝቡ ተስፋ የሚሰጥ የፍትሕ ሥርዓትን ለመዘርጋት በሚደረገው ጥረት የትብብር ጥምረቱ አባል ተቋማት በተጠያቂነት መንፈስ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። የትብብር ጥምረቱ ዘርፉን በሚቀይሩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንደሚጠበቅበት ነው ፕሬዝዳንቱ ያነሱት። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ባለፈው በጀት ዓመት ሰፊ ተግባራትን ሲከውን እንደቆዬ ያነሱት አቶ ዓለምአንተ በተሠራው መልካም ተግባርም የክልሉ ምክር ቤት የሰጠው ዕውቅና ማሳያ ነው ብለዋል። የትብብር ጥምረቱ በቀጣይም በበቂ በጀት ታግዞ ከዚህ በላይ ለፍትሕ መስፈን መሥራት እንደሚጠበቅበት ጠቁመዋል።
ጥምረቱ ከዚህ በፊት የነበሩ ጥንካሬዎችን በማስቀጠል እና ክፍተቶችን በትኩረት በመሙላት ለክልሉ ሁለንተናዊ ሰላም እና ፍትሕ መሥራት እንደሚጠበቅበትም አንስተዋል። የትብብር ጥምረቱ የማይናቅ እና በርካታ የፍትሕ ማስፈን ተግባራትን በማከናወን በኩል ሥራዎችን እያከናወነ እንደኾነ በተወያዮች ተነስቷል። በቀጣይም የነበሩ ችግሮችን የጋራ በማድረግ ከዚህም በላይ ለፍትሕ መስፈን በቅንጅት መሥራት እንደሚያስፈልግ በአጽንኦት ተመላክቷል።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየጎርፍ አደጋ ለክልሉ ሥጋት እንዳይኾን እየተሠራ ነው፡፡
Next articleበበጀት ዓመቱ ከ15 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ የቤተሰብ አባላት የጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚ ኾነዋል።