የጎርፍ አደጋ ለክልሉ ሥጋት እንዳይኾን እየተሠራ ነው፡፡

6
ባሕር ዳር: ነሐሴ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ጎርፍ የማኅበረሰቡ ስጋት እንዳይኾን በቅንጅት እየተሠራ መኾኑን የክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን አስታውቋል፡፡ በደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ የሽና ቀበሌ ነዋሪ አቶ ምናለ ጎሹ ቀደም ሲል የጉማራ ወንዝ በክረምት እየሞላ ይቸገሩ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ መንግሥትም ይህን ችግር ተገንዝቦ የጎርፍ መከላከያ ክትር በመስራቱ ከጉዳት ታድጓቸው እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ ይሁንና በ2017 ዓ.ም የጎርፍ መከላከያ ክትሩ ጥገና ስላልተደረገለት ሥጋት ላይ መውደቃቸውን ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡
በፎገራ ወረዳ የኮኪት ጎጥ ነዋሪ አመራ ታዴ በእነርሱ አካባቢ ቋሚ የጎርፍ መከላከያ አለመሠራቱን ገልጸዋል፡፡ ዘንድሮም ለጎርፍ አደጋ ልንዳረግ እንችላለን የሚል ሥጋት አድሮብናል ነው ያሉት። የጎርፍ አደጋ እንዳይከሰት ድጋፍ እንዲደረግም ጠይቀዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ በላይ አስራደ በደራ፣ ፎገራ እና ሊቦ ከምከም ወረዳዎች የሚገኙ 23 ቀበሌዎች በጎርፍ ሊጠቁ ይችላሉ ተብለው መለየታቸውን ገልጸዋል፡፡ በበጋ ወቅት 25 ሚሊዮን ብር በመመደብ 100 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የጎርፍ መከላከያ ሥራዎች ተሠርተዋል ነው ያሉት፡፡ ችግሩ ቢደርስ ተጋላጭ የሚኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሊወጡባቸው የሚችሉባቸው ጀልባዎች ተዘጋጅተዋል ያሉት ኀላፊው የሰፈራ ቦታዎችም ተለይተዋል ብለዋል።
እስካሁን ባለው የክረምቱ ሁኔታ በርብ፣ በጣና ዲንቢሶ እና በሊቦ ከምከም አካባቢዎች በጎርፍ የተጎዳ ሰብል መኖሩን አንስተዋል። አሁንም የጎርፍ የአደጋ ስጋት እንዳለ አመላክተዋል።ከርብ ግድብ ያልተመጠነ ውኃ በመለቀቁ በ65 አርሶ አደሮች ቤት ላይ ጎርፍ መግባቱን የጠቆሙት ኀላፊው የሚመለከተው አካል ጥንቃቄ መውሰድ እንዳለበት አሳስበዋል።የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽንም እስካሁን ያከናዎነው ሥራ እንዳለ ኾኖ አደጋ ከመድረሱ በፊት ተጨማሪ በጀት በመመደብ፣ ተጨማሪ የመጠለያ ድንኳን ማዘገጃት እንዳለበት አንስተዋል።
በዞኑ የስጋት ቀጣና ውስጥ የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችም ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል። በአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ እና የአስቸኳያ ጊዜ ምላሽ ዳይሬክተር ብርሃኑ ዘውዱ በክልሉ 486 ቀበሌዎች እና 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ወገኖች ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ መኾናቸው በጥናት መለየታቸውን አንስተዋል።
ለአደጋ ማቅለያ ሥራዎችም 400 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ በጥናት መመላከቱን የተናገሩት ዳይሬክተሩ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ወረዳዎች በመምረጥ በ145 ሚሊዮን ብር የቅድመ መከላከል ሥራ ተከናውኗል ብለዋል። ለጎርፍ አደጋ ይበልጥ ተጋላጭ ይኾናሉ የተባሉ 24 ወረዳዎች መለየታቸውንም ገልጸዋል። ግድቦች ሞልተው ወደ ኅብረተሰቡ እንዳይፈሱ ዳርቻቸውን የማሳደግ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት፡፡ ከግድቦች ውኃ ሲለቀቅም በጥንቃቄ ነው ብለዋል፡፡
የጎርፍ ማፋሰሻ ቦዮችን እና መቀልበሻዎችን በመገንባት ሊደርስ የሚችልን አደጋ አስቀድሞ መከላከል የሚያስችሉ ሥራዎች መከናዎናቸውንም አመላክተዋል። ወደ ጣና ሐይቅ ከሚፈሱ ወንዞች መሙላት እና መፍሰስ ጋር በተያያዘም በደራ፣ ፎገራ፣ ሊቦ ከምከም ወረዳዎች እና ወረታ ከተማ አሥተዳደር ሊደርስ የሚችልን የጎርፍ መጥለቅለቅ ለመታደግ ሥራዎች መከናዎናቸውን ገልጸዋል።
ማኅበረሰቡም የጎርፍ ማፋሰሻ ቦዮችን በመሥራት እና በማጽዳት ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡
እንደ ክልል ከክረምቱ ጋር ተያይዞ ለአደጋ ምላሽ ተብሎም ምግብ እና ምግብ ነክ ቁሳቁስ፣ የሕይዎት አድን ጀልባዎች እና ልዩ ልዩ የግብዓት አይነቶች በቅንጅት ተለይተው ዝግጁ መደረጋቸውን አመላክተዋል።
ዘጋቢ፡- ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleየደብረ ብርሃን ከተማ የሕዝብ የመልማት ጥያቄዎች በቅደም ተከተል ምላሽ እየተሰጠባቸው ነው።
Next articleየፍትሕ ሥራ አንድ ቦታ ላይ የሚያልቅ አይደለም።