
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 30/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኮሮና ቫይረስ ወረርሸኝን ለመከላከል የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች በከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ሳይለብሱ መንቀሳቀስ እንደማይችሉ የአብመድ የጋዘጠኞች ቡድን ታዝቧል፡፡ በሌላ ጎኑ ምንጃር ሸንኮራ፣ አሳግርት፣ ሀገረማሪያም ከሰም እና በረኸት ወረዳዎች ደግሞ መዘናጋት በብዛት ታዝበናል፡፡ የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ለብሶ የሚጓዘውን ለመዘነጥ እንደለበሰ የመቁጠር ልማዶችንም ተመልክተናል፡፡
ደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ላይ ግን ሰዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ለብሰው እንደሚንቀሳቀሱ በየመንገዶቹ ተዘዋውረን ተመልክተናል፡፡ ከነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ አነጋገር ፍርዱ በከተማ ውስጥ ሁሉም ሰው የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ለብሶ እንዲሄድ ትምህርት መሰጠቱንና ሰውም በአብዛኛው ትምህርቱን ተቀብሎ መተግበሩን ገልጸውልናል፡፡ አብዛኛው ቢጠነቀቅም አሁንም መዘናጋት እንዳለም አስረድተዋል፡፡ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ አለባበስ ላይ ጉድለት መኖሩንም ወይዘሮ አነጋገር ገልጸዋል፡፡ አንዳንዶች ከአፍንጫ በታች ዝቅ አድርጎ መልበስ፣ መኪና ውስጥ እና ሆቴል ሲገባ አውልቆ መቀመጥ እንደታዘቡም ገልጸዋል፡፡
የሕዝቡን አኗኗር ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገበ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ደግሞ የሕግ አካላት መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ ሕዝቡም ለራሱ ሲል ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ያሳሰቡት ወይዘሮ አነጋገር እርሳቸው የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ ከቤት ውጭ ተንቀሳቅሰው እንደማያውቁም ተናግረዋል፡፡
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የሰላም እና የሕዝብ ደኅነነት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መቶ አለቃ ጭንቅል ጉችማ ኅብረተሰቡን ከወረርሽኙ ለመከላከል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እየተተገበረ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የኅብረተሰቡን የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ አለባበስ ሁኔታ ለመለካት ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች በተደረገ ጥናት 98 በመቶው ሰው የአፍ እና አፍንጫ መሸፍኛ ለብሶ እንደሚሄድ መረጋገጡንም አስታውቀዋል፡፡ አሁንም የአፍ እና አፍንጫ የማይለብሱ ሰዎችን ለማስተማር እየተሠራ እንደሆነ አስታውቀዋል፤ ሰው ለሕግ መከበር ብሎ ብቻ ሳይሆን ለራሱ እና ለቤተሰቡ ደኅንንት ሲል መልበስ እንዳለበትም መክረዋልል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ ዋጁ የከለከላቸውን ጥፋቶች ፈፅመው የተገኙት ከ900 በላይ በአነስተኛ የንግድና የወንጀል ተግባር ላይ ተሰማርተው የተገኙ አካላት ትምህርት መሰጠቱንም አስታውቀዋል፡፡ የፑል ቤቶች፣ ጫት ቤቶች፣ ሺሻ ቤቶች፣ ጭፈራ ቤቶች፣ አርቄ ቤቶች ላይ የተሰማሩ ናቸው ትምህርት የተሰተጣቸው፡፡ 38 ሰዎች ደግሞ ከጥፋታቸው መታረም ስላልቻሉ 54 ሺህ 44 ብር ተቀጥተዋል ተብሏል፡፡
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ደስታ አንዳርጌ ከተማዋ ለአዲስ አበባ ካላት ቅርበትና በርካታ የኢንቨስትመንት ሥራዎች የሚገኙባት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለወረርሽኙ ላለመጋለጥ ማኅበረሰቡ የጀመረውን የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ የመልበስ መልካም ልምድ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡
ወረርሽኙን ለመከለካል እስካሁን 35 ሺህ ቤቶችን በመዳሰስ 90 ሺህ ሰዎችን የመለየት ሥራ እንደተሠራም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ደስታ አስረድተዋል፡፡ የመከላከሉ ሥራ ደግሞ የአገር ሽማግሌዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችን፣ ባለሀብቶችን፣ ሆስፒታሉንና ዩኒቨርሰቲዎችን በማማከር እየተሠራ ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡ ሁሉም ሰው የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ መልበስ እንዳለበት ያስገነዘቡ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ደስታ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ገዝተው መልበስ ለማይችሉ ዜጎች የከተማ አስተዳደሩ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመሆን ገዝቶ ለማቅርብ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል፡፡
‘‘መዘናጋት በሌላው ሀገር ላይ መሥዋዕት ሲያስከፍል ዓይተናል፤ የግንዛቤ ፈጠራውን በየቀኑ እንሠራለን፤ ቅድሚያ ማስተማር ላይ እየሠራን ነው፤ ወደ ርምጃ አልገባንም፤ ዓይናችንን እያየ ሰው እንዲሞት ግን አንፈቅድም፡፡ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ መልበስ ግዴታ ነው፤ የሚደራደር የሕግ አካልም አይኖርም፤ ኬላዎች ላይ አስፈላጊ ጥንቃቄ እያደረግን ነው’’ ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ደስታ አንዳርጌ ኅብረተሰቡ ደግሞ እንደ ግለሰብ መወጣት ያለበትን ኃላፊነት መወጣቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው -ከደብረ ብርሃን
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡