
ደብረ ብርሃን: ነሐሴ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ብርሃን ከተማ ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤት አባላት የመራጭ ተመራጭ የምክክር መድረክ እያካሄዱ ነው።
በውይይቱ ከአሁን በፊት ተጠይቀው ምላሽ ያገኙ እና በቀጣይ ምላሽ ቢሰጥባቸው የተባሉ ጥያቄዎች ቀርበው ውይይት ተደርጓል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የደብረ ብርሃን ከተማ ተወካይ ወይዘሮ ገነት ቤተ በማኅበረሰቡ ተጠይቀው የነበሩ የመልማት ጥያቄዎች በቅደም ተከተል እየተፈቱ ነው ብለዋል።
ለአብነትም ከአዲስ አበባ ደብረ ብርሃን የፍጥነት መንገድ በቀጣይ አምሥት ዓመት እንዲሠራ በዕቅድ መያዙ፣ ከደብረ ብርሃን ለሚ መገንጠያ ያለው የአስፋልት መንገድ ግንባታ ከደብረ ብርሃን ጀምሮ እንዲገነባ መደረጉ፣ በከተማው ያሉ ያረጁ የኤሌክትሪክ መስመር መቀየር፣ አራት የገጠር ቀበሌዎችን የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል። በማኅበራዊ ዘርፍም የደብረ ብርሃን ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሲቲ ስካን ግዥ እና የአጠቃላይ ሆስፒታል ግንባታ ምላሽ ያገኙ ጥያቄዎች ናቸው ብለዋል።
በኢኮኖሚው ዘርፍ የኮሪደር ልማት ግንባታ፣ የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣ የዋጋ ማረጋጋት፣ የገበያ ማዕከላት ግንባታ እና ሌሎችም ተግባራት ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል ተብሏል። ተሳታፊዎችም ለተሠሩት ሥራዎች አመሥግነው በቀጣይ መፈታት አለባቸው ያሏቸውን ጥያቄዎች አቅርበዋል። የሰላም እና ጸጥታ፣ የኑሮ ውድነት የከተማ የውስጥ ለውስጥ የመንገድ ግንባታ፣ የንጹህ መጠጥ እና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ችግሮች መፈታት አለባቸው ብለዋል።
ዘጋቢ፡- ለዓለም ለይኩን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን