
ባሕር ዳር: ነሐሴ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አስማረ ደጀን (ዶ.ር) እንዳሉት ኢንስቲትዩቱ የምርምር ሥራዎችን እና አዳዲስ ተክኖሎጅዎችን በማፍለቅ እያስተዋወቀ ይገኛል። የሚያወጣቸውን መነሻ ዘሮች ያሰራጫል፤ የአቅም ግንባታ ሥራ እየሠራም ይገኛል። ኢንስቲትዩቱ በ2016/17 ዓ.ም ለመሥራት ካቀደው 584 የምርምር ሥራዎች ውስጥ 83 በመቶ የሚኾኑትን መሥራቱን ገልጸዋል። የምርምር ሥራዎቹ ሰብል፣ እንስሳት፣ አፈር እና ውኃ አያያዝ፣ ደን፣ የዘር ብዜት እና የተለያዩ ምርምሮችን ያካተቱ ናቸው።
ባለፉት ዓመታት ምርምር የተደረገባቸው ዘጠኝ የሰብል ዝርያዎች መለቀቃቸውንም ነው የገለጹት። ከተለቀቁ ዝርያዎችም አንዱ “እንቁ ዳጉሳ” ነው። እንቁ ዳጉሳ በዝናብ አጠር አካባቢዎች ፈጥኖ በመድረስ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችል ዓይነተኛ ሰብል ነው። ምርታማነታቸው አንደኛው የተሻሻለው ዝርያ በሄክታር 17 ነጥብ 2 ኩንታል፣ ሁለተኛው የተሻሻለው ዝርያ ደግሞ 20 ነጥብ 8 ኩንታል የሚሠጡ ናቸው።
ሌላው በምርምር ከተለቀቁት ውስጥ ሦስት የማሽላ ዝርያዎች ይገኙበታል። “ሲሪንቃ አንድ” የተባለው የማሽላ ዝርያ በሄክታር 52 ኩንታል የሚሰጥ ሲኾን ከበፊቱ ማወዳደሪያ ዝርያ 30 በመቶ የምርት ብልጫ አለው።
ሌላኛው “ወለዲ” የተባለው የማሽላ ዝርያ ሲኾን በሄክታር 47 ኩንታል የሚሰጥ ነው። ከበፊቱ የማወዳደሪያ ዝርያ ደግሞ 29 በመቶ ብልጫ አለው።ሦሥተኛው “ዳግም” የተባለው የማሽላ ዝርያ ሲኾን በሄክታር 44 ኩንታል ይሰጣል። ከተሻሻለው የመወዳደሪያ ዝርያ ደግሞ 20 በመቶ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል። አንደኛው ዝርያ ፈጥኖ መድረስ የሚችል ሲኾን ሁለቱ ደግሞ በመካከለኛ ጊዜ የሚደርሱ ናቸው፡፡
ሌላኛው የተለቀቀው “ዛቲ” የተባለ የጤፍ ዝርያ ነው፡፡ በሄክታር 25 ኩንታል ምርት የሚሰጥ እና ከተሻሻለው ማወዳደሪያ ዝርያ ደግሞ 20 በመቶ የምርት ብልጫ አለው ተብሏል። በስሪንቃ፣ ጃሪ፣ ጨፋ፣ ዓለም ከተማ፣ ሰቆጣ እና ተመሳሳይ ቦታዎች መመረት የሚችል መኾኑ ተረጋግጧል፡፡ ለእርጥበት አጠር አካባቢዎችም ተስማሚ፣ ነጭ የዘር ቀለም ያለው፤ የተሻለ ቁመት እና ዛላ ብሎም ክብደት ያለው ነው።
ሌላኛው “የምስራች” የተባለ የምስር ዝርያ ሲኾን በሄክታር 19 ኩንታል ምርት የሚሰጥ እና ከአካባቢው ማወዳደሪያ ዝርያ 57 በመቶ የምርት ብልጫ አለው። በወረኢሉ፣ በለገሂዳ፣ በጃማ፣ በእነዋሪ፣ በዳውንት እና ተመሳሳይ ቦታዎች መመረት የሚችል መኾኑም ተረጋግጧል፡፡ ቀድሞ የሚደርስ እና ድርቅን የሚቋቋም፣ የተሻለ ምርት መስጠት የሚችል “ሰርክ” የተባለ ለሽሮ መኾን የሚችል የአተር ዝርያም ተለቅቋል፡፡ በሄክታር እስከ 28 ኩንታል ምርት መስጠት የሚችል ነው። ከአካባቢው ማወዳደሪያ ዝርያ በ27 በመቶ የምርት ብልጫ አለው። በወረኢሉ፣ ጃማ፣ መቄት፣ አዴት እና ተመሳሳይ ቦታዎች መመረት የሚችል መኾኑም ተረጋግጧል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን