
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአካል ጉዳተኞችን ችግሮች ለመፍታት እና መብቶቻቸውን ለማስከበር በፌዴሬሽኑ አማካኝነት የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ገልጿል። የባሕር ዳር ከተማ ሴቶች እና ሕጻናት መምሪያ የማደራጃ ባለሙያ ትዕግስት ሙጨ አካል ጉዳተኞች ከዚህ ቀደም በድብቅ ይኖሩ እንደነበር ተናግረዋል።
አሁን ግን የፌዴሬሽኑ አባል በመኾን ችግሮቻቸውን በተወሰነ መልኩ እየፈቱ መኾናቸውን ነው ያስረዱት። የመኖሪያ ቤት እና የሥራ ቅጥር ጥያቄያቸውን በፌዴሬሽኑ በኩል ምላሽ እንዲያገኝ መደረጉንም አብራርተዋል። የአጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ የአካል ጉዳተኞች ሠብሣቢ የቻለ ፍቃዴ በፌዴሬሽኑ አባል በመኾን የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው እና ቤተሰቦቻቸውንም መርዳት እንደቻሉ ገልጸዋል። ወደ ማኅበሩ ያልመጡ እና በቤት ውስጥ የሚገኙ አካል ጉዳተኞች ከፌዴሬሽኑ ጋር በመደራጀት የሥራ፣ የብድር እና የሌሎች ዕድሎች ተጠቃሚ ሊኾኑ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ሠብሣቢ ዳንኤል አበበ አካል ጉዳተኞችን በኢኮኖሚው ዘርፍ ተሳታፊ እና ተጠቃሚ ለማድረግ ከከተማ አሥተዳደሩ እና ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር በመተባበር የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ተናግረዋል። ለወደፊቱም አካል ጉዳተኞች መብቶቻቸውን እንዲያውቁ፣ ራሳቸውን እንዲችሉ እና ተምረው ሥራ ያላገኙት ወደ ሥራ ዓለም እንዲቀላቀሉ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ አብራርተዋል።
የአማራ ክልል የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ፍሬሰላም ዘገየ ፌዴሬሽኑ የአካል ጉዳተኞችን ድምጽ ለማሰማት በሁሉም ዞኖች እና ወረዳዎች ቅርንጫፎችን እየከፈተ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በቀጣይም አካል ጉዳተኞችን የሚጠቅሙ አስገዳጅ ሕጎች እንዲወጡ ትኩረት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
በተጨማሪም የሕንፃ አዋጁን መሠረት በማድረግ ሕንፃዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አድርገው እንዲገነቡ ሢሠራ መቆየቱን ጠቁመዋል። ለሁሉም አካል ጉዳተኞች በመኖሪያ ቤት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚሠራም አስረድተዋል። የሥራ ዕድል ፈጠራ አሠራሩ አካል ጉዳተኞችን አካታች እንዲኾን፣ የሥራ ቦታዎቹ ምቹ፣ ተደራሽ እንዲኾኑ እና ምሩቃን በቀጥታ ወደ ሥራ እንዲመደቡ በፌዴሬሽኑ በኩል በትኩረት እንደሚሠራ ተገልጿል። ይህ ሥራ ውጤታማ እንዲኾን የመንግሥት አካላት፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ማኅበረሰቡ እና የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸውም ተመላክቷል።
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!