
ደብረ ብርሃን: ነሐሴ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ ዞን የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱ የማድረግ ተግባሩ ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበበት እንደሚገኝ የሰሜን ሸዋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኤልያስ አበበ ገልጸዋል።
የትጥቅ ትግል መርጠው ወደ ጫካ የገቡትን ወገኖች ወደ መደበኛ ሕይወታቸው በመመለስ ሂደቱ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የፖለቲካ መሪዎች እና የጸጥታ መዋቅሮች የጋራ ጥረት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።
የ2018 በጀት ዓመት ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ከ 1 ሺህ 300 በላይ ታጣቂዎች የሰላምን አማራጭ ተቀብለው ከነሙሉ ትጥቃቸው ወደ አካባቢያቸው ተመልሰዋል ነው ያሉት።
ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን መቀበላቸው የሕዝቡን የልማትና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ እድል እየፈጠረ መኾኑን አንስተዋል።
የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ለተቀበሉ ታጣቂዎች ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ፣ በአግባቡ ሥልጠና በመስጠት እና ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ በማድረግ አካባቢያቸውን በተደራጀ አግባብ እየጠበቁ ሥራቸውን እንዲከውኑ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯልም ነው ያሉት።
ኅብረተሰቡም በጸጥታ ችግሩ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት መቆየቱን ያነሱት ኀላፊው የሰላም አማራጭን ለተቀበሉ ታጣቂዎች ጥሩ አቀባበል እያደረገላቸው መኾኑንም ገልጸዋል። እርስ በእርስ መገዳደል ከተራዘመ ችግር ያለፈ ጥቅም አይገኝበትም ነው ያሉት።
በሰሜን ሸዋ ዞን በሚገኙ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሱ ያሉ ታጣቂዎችን የሰላምን አማራጭ እንዲቀበሉ የማድረግ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመልክተዋል።
መንግሥት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ በማይቀበሉት ላይ ደግሞ የተጠናከረ ሕግ የማስከበር ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን