
ደብረ ታቦር፡ ነሐሴ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የተመሠረተበትን 30ኛ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ ይገኛል። ይህንን በማስመልከት በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች በማገልገል ላይ የሚገኙ የደቡብ ጎንደር ዞር የመንግሥት ሠራተኞች ስለ አሚኮ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ)
በአማራ ክልል የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር በማርገብ ክልሉ ወደ ሰላም እንዲመለስ የማይተካ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል።
ለዚህም በየጊዜው የተካሄዱ ሕዝባዊ ውይይቶችን እና ሀገራዊ ምክክሮችን በማሳያነት አንስተዋል። አሚኮ ስለ ሰላም አይተኬ ሚናን ተጫውቷል ነው ያሉት።
አሚኮ በርካታ የለውጥ ሂደቶችን ያሳዬ ተቋም ነው ያሉት አስተያየት ሰጪያችን አድጎ ጫኔ በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ ልማቶች ለማኅበረሰቡ ያላቸውን ሁለንተናዊ ጥቅም እያሳዬ መኾኑን ተናግረዋል።
በተለይ ደግሞ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር በውይይት እንዲፈታ ለማድረግ የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራንን እና የሀገር ሽማግሌዎችን በመጋበዝ በሰላሙ ዙሪያ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣ ተቋም ነው ብለዋል።
ያጋጠመውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት ትልቅ ሥራ ሠርቷል ያሉት ደግሞ እፀገነት ሲሳይ ናቸው። ከሕዝብ ጋር በቅንጅት በመሥራት ክልሉ ወደ ሰላም መንገድ እንዲመጣ በሰፊው ሠርቷል ነው ያሉት።
በቀጣይም በሰው ኃይልም ኾነ በቴክኖሎጂ የበለጠ ተጠናክሮ በሌሎች የክልሉ ከተሞች እንዳሉት የስርጭት ጣቢያዎች ሁሉ በደቡብ ጎንደር ዞን ያለውን ተደራሽነት ከዚህ በላይ ማሳደግ፣ ማገልገል እና ተደማጭነቱንም ማስፋት ይገባዋል ብለዋል።
አሚኮ የማኅበረሰቡ ድምጽ ነው ያሉት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ ተስፋዬ አያሌው ናቸው። ቀደም ሲል በሬዲዮ፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ባሉት አማራጮች ሁሉ ዝግጅቶችን እንደሚከታተሉ ተናግረዋል። በእነዚህ ዓመታትም የስርጭት አድማሱን በዚያው ልክ ማስፋቱን ነው የገለጹት።
ተቋሙ በዝግጅቶቹ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፓለቲካዊ ይዘቶችን በስፋት እንደሚዳስስ ተናግረዋል።
አሚኮ የሚሰጠው መረጃ ጥልቀት ያለው እና አስተማሪ መኾኑን ሌላዋ ሀሳባቸውን ያጋሩን ፋሲካ ሹምየ ተናግረዋል። አሚኮ በርካታ የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጉዳዮችን ነቅሶ በማውጣት መረጃን ለማኅበረሰቡ ተደራሽ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
በተለይ ደግሞ በትምህርት ዘርፍ ማኅበረሰቡ ሰፊ ግንዛቤ እንዲኖርው ያደረገ ሚዲያ እንደኾነ ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን ያጋሩን የመንግሥት ሠራተኞች “የአሚኮ የ30 ዓመት የለውጥ ጉዞዎች የመጡት ባለው የሰው ኀይል በመኾኑ ለመላው የአሚኮ ሠራተኞች እንኳን አደረሳችሁ” ብለዋል። በቀጣይም አሚኮ የተሻለ የስኬት ጉዞ እንዲገጥመው መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!