የደሴ ከተማ አሥተዳደር ለ2018 የትምህርት ዘመን ከ69 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ አቅዶ እየሠራ ነው።

20

ደሴ: ነሐሴ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ የ2018 ትምህርት ዘመን ምዝገባን ለማካሄድ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

በውይይቱ የ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የትምህርት ተደራሽነት እና ተሳትፎን በተመለከተ የነበሩ መልካም ተግባራት እና ክፍተቶች ተነስተው ውይይት ተደረጎባቸዋል፡፡

የነበሩ ጥንካሬዎችን በማስቀጠል እና ክፍተቶችን በማረም ለ2018 የትምህርት ዘመን በግል እና በመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎችን በአጭር ጊዜ እንዲመዘገቡ ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸው ተጠቁሟል፡፡

የደሴ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ፍቅር አበበ እንዳሉት በ2018 ዓ.ም ከ69 ሺህ በላይ ተማሪዎች እንደሚመዘገቡ ይጠበቃል።

የትምህርት ቤቶችን ገጽታ መቀየር እና ምቹ ማድረግ በክረምት ሥራዎች ትኩረት እንደተሰጣቸው የገለጹት ኀላፊው ለመጪው የትምህርት ዘመን 44 አዳዲስ የመማሪያ ክፍሎች ተገንብተው 12ቱን መረከባቸውን ጠቅሰዋል፡፡

አሚኮ ያነጋገራቸው ርእሰ መምህራን እና ሱፐርቫይዘሮች በበኩላቸው የባለፈው የትምህርት ዘመን ክፍተቶች እንዳይደገሙ በቅንጅት እየሠሩ መኾናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን በወቅቱ እና በተገቢው ጊዜ በማስመዝገብ ወደ ትምህርት ገበታ የመላክ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ በመድረኩ ተጠይቋል፡፡

በከተማ አሥተዳደሩ በሁሉም ትምህርት ቤቶች መስከረም 05/2018 ዓ.ም ትምህርት እንደሚጀመር ተመላክቷል።

ዘጋቢ:- ደጀን አምባቸው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የመራጮች ድምጽ መስጫ ቀንን ይፋ አደረገ።
Next articleአሚኮ ስለ ሰላም አይተኬ ሚናን ተጫውቷል።