
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 30/2012 ዓ.ም (አብመድ) በዓባይ ወንዝ አጠቃቀም እና በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ ያተኮረ ውይይት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ትናንት ተካሂዷል።
በውይይቱ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሲቪልና ምሕንድስና ፋኩሊቲ ረዳት ፕሮፌሰር ዳኛቸው አክሎግ (ዶክተር) የኢትዮጵያን የውኃ መጠን፣ የሀብት አጠቃቀም እና ዓለም ዓቀፍ ተሞክሮዎችን መሠረት ያደረገ የውይይት መነሻ ሐሳብ አቅርበዋል። ኢትዮጵያ ባላት ፀጋ ልትለማ የምትችለው የግድቦቿን ቁጥር ስታሳድግ እና ውኃዋል ለልማት ስታውል መሆኑ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ሐሳብ አመላክተዋል።
ዶክተር ዳኛቸው እንዳሉት ኢትዮጵያ ካላት መልክአ ምድር፣ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ እና ችሮታ አንጻር ከውኃ እና አፈር ውጭ ብዙ የተፈጥሮ ሀብት የላትም። ምንም እንኳን ኢትዮጵያ የውኃ ማማ እየተባለች ብትጠራም የውኃ ሀብት አጠቃቀሟ ካላት የሕዝብ ብዛት ጋር ሲነጻጸር እጥረት እንዳለበት አስገንዝበዋል። ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መለኪያ መስፈርት መሠረት የውኃ እጥረት ያለባቸው በሚባልበት ደረጃ ላይ እንደምትገኝም አመላክተዋል።
የሀገሪቱ ውኃ በብዛት የሚመነጨው በምዕራባዊ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ነው። ኢትዮጵያ ካላት አጠቃላይ ውኃ መካከል ደግሞ ወደ ዓባይ የሚፈስሱት ወንዞች 70 በመቶውን ይሸፍናሉ። እነዚህ ወንዞች ሀገር አቋርጠው የሚስሱ ናቸው፤ የኢትዮጵያ የመጠቀም ሁኔታ ግን በጣም አናሳ ሆኖ መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዝናብ ተኮር ግብርና ላይ የተመሠረተ ነው። አብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች በተለይም ምሥራቅ እና ሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች በቂ ዝናብ የማያገኙ ናቸው። በዚህ የተነሳም ሕዝብ ለተደጋጋሚ ድርቅ እና ረሀብ እንደተጋለጡ በማብራሪያቸው አሳይተዋል።
የበለጸጉ ሀገራት ውኃቸውን ተጠቅመው ኢኮኖሚያቸውን እንደገነቡ ያነሱት ዶክተር ዳኛቸው ኢትዮጵያም መልማት የምትችለው የውኃ ሀብቷን በአግባቡ ስትጠቀምና የግድቦቿን ቁጥር ስታሳድግ መሆኑን ተናግረዋል። በዓለም ላይ ወደ 46 ሺህ ግድቦች እንዳሉ ያስታወቁት ዶክተር ዳኛቸው ከዚህ ውስጥ ግን ግማሽ ያህሉ የቻይና መሆናቸውንና ለዕድገቷ ጉልህ ሚና መጫወታቸውን አሳይተዋል። ጃፓን ብቻ ወደ ወደ 2 ሺህ የሚጠጉ ግድቦች እንዳሏትም ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ግን 35 ግድቦች ብቻ እንዳሏት ነው ያመለከቱት።
ያለውን የውኃ ሀብት መጠቀም ያላስቻሉ ችግሮችንም ዶክተር ዳኛቸው ዘርዝረዋል። አብዛኞቹ ወንዞች ድንበር ተሻጋሪ መሆናቸው እና ከሀገራቱ ጋር ቋሚ የውኃ አጠቃቀም ስምምነት አለመኖሩ የውኃ ፖለቲካዊ ችግር እንዲኖር አድርጓል። ይህም በኢኮኖሚዋ ዝቅተኛ ለሆነችው ኢትዮጵያ ለግድብ ብድር እንዳታገኝ አድርጎ እንደቆየ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ አመቺ አለመሆን እና ስለውኃ ሀብት በጥናት የተደገፈ በቂ መረጃ አለመኖርም እንደ ቴክኒካል ችግር ሆነው መኖራውቸንም አመላተዋል። ዓባይ ቶሎ እንዳይገደብ የኢኮኖሚ ችግር በትልቁ የሚነሳ መሆኑን በማመላከትም ሌሎችም ውስጣዊ ፖለቲካዊ ችግሮች እና ውጫዊ ተፅዕኖዎች ተያያዥ ችግሮች ሆነው እንደነበር ነው ያመለከቱት። ቀደም ባሉት ጊዜያት በዘርፉ በቂ የተማረ የሰው ኃይል አለመኖር፣ በዘርፉ ችግር ፈቺ የምርምር ሥራ በበቂ ሁኔታ አለመሠራቱ እና የተሠሩትንም ለሕዝብ ተደራሽ የሚያደርግ ጠንካራ የመረጃ ቋት አለመኖር እንደክፍተት መታየታቸውንም ገልጸዋል።
“ችግር እንዳለብን ማወቅ ወደ መፍትሔው ለመሄድ ግማሽ መንገድ ያቀርባል” ያሉት ዶክተር ዳኛቸው ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ችግሩን በመረዳት የጥቁር ዓባይ ውኃ ተቋምን (ብሉ ናይል ወተር ኢንስቲትዩት) መሥርቶ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል። ተቋሙ ውኃ እና ከውኃ ጋር ተዛማጅ የሆኑ ምርምሮችን የሚሠሩ አምስት የምርምር ክፍሎች አሉት። ዘላቂ እና የሀገርን ተጠቃሚነት ሊያሳድግ በሚችል መልኩ በሀገር አቀፍ ደረጃ ጠንካራ የውኃ ተቋም ማቋቋም እንደሚገባም መክረዋል።
ምንም እንኳን ኢትዮጵያ 35 ግድቦች ቢኖሯትም በውኃ መጠን የግብጹን አስዋን ግድብ 10 በመቶ እንኳን ድርሻ ላይሸፍኑ እንደሚችሉ የውይይቱ ተሳታፊዎች ተናግረዋል። ውኃን በምን ያህል ጥቅም ላይ ማዋል እንደተቻለ ማሳያው የሚፈስሰውን ውኃ ማቆም ሲቻል መሆኑንም ተናግረዋል። አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ወንዞች ድንበር ተሻጋሪ መሆናቸውንንና በታችኞቹ ሀገራት ጥያቄ ሊነሳባቸው የሚችሉ መሆኑን ያነሱት የውይይቱ ተሳታፊዎች ‘‘ኢትዮጵያ የውኃ ማማ ነች’’ እያሉ እንዳትጠቀም ለሚከራከሩ የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት የድርሻዋን የመጠቀም መብት እንዳላት ማሳወቅ እንደሚገባ መክረዋል። ውኃን መገደብ ከኃይል ማመንጫነት በተጨማሪ ለግብርና፣ ለቱሪዝም እና ዓሣ ሀብት ልማት እንደሚጠቅም አድርጎ ማሰብ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡