“ታሪኩን የማያከብር ትውልድ መቼም ታሪክ አይሠራም” ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ

21

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሴኔት ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም በማራኪ ግቢ የሚገኘውን የፊልም ትምህርት ክፍል አዳራሽ “ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ሲኒማ አዳራሽ” ብሎ ሰይሟል። ለመኾኑ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ማን ናቸው?

👉 ትውልድ

ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ የተወለዱት በጎንደር ከተማ በ1938 ዓ.ም ነው። አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በቀድሞው ልዕልት ተናኘ ወርቅ የአሁኑ ኅብረት ትምህርት ቤት ነው የተማሩት።

ዕውቁ ደራሲ እና አርበኛ አባታቸው ገሪማ ታፈረ እንዲሁም እናታቸው መምህርት ሶፍያ አሁን ለደረሱበት ደረጃ እና የሕይዎታቸው ጉዞ ድርሻቸው ከፍ ያለ እንደኾነ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ይናገራሉ።

👉 የትምህርት እና የፊልም ሥራ ጊዜ

በ1959 ዓ.ም ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በፈጠራ ጥበብ ማዕከል ውስጥ አጭር ቆይታ ካደረጉ በኋላ በልጅነታቸው የፊልም ተዋናይነት እና ደራሲነትን ለመማር ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ሰሜን አሜሪካ አቅንተው የአንደኛ እና የሁለተኛ ዲግሪያቸውን አጠናቅቀዋል።

በዚያ በተማሪነት ዘመናቸው ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ሁለት ፊልሞችን ማለትም ሐወር ግላስ (“Hour Glass” በ1963 ዓ.ም) እና ቻይልድ ኦፍ ሪዚስታንስ (“Child of Resistance” በ1964 ዓ.ም) የተሰኙ ፊልሞችን መድረስ ችለዋል።

በመጨረሻም መመረቂያ ፊልማቸውን ስለ እንዲት ሴት ልጅ እናት እና ነፍሰ ጡር ጥቁር አሜሪካዊት ስለሚደርስባት በደል ብሎም ስለምትኖርበት የድህነት አረንቋ እና ቡሽ ማን (“Bush mama”) የተሰኙ ፊልሞችን ሠርተዋል።

በእነዚህ ጊዜያቶች ነው ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ የፊልም ዳይሬክተር ብቻም ሳይኾኑ ታሪክ ተራኪ፣ በፊልም ሥራቸው ለሰው ልጅ ክብር እና መብት ለሚደረግ ትግል በተለይም ለአፍሪካ ብሎም በዓለም ላይ ተበትኖ ለሚኖረው ጥቁር ሕዝብ ፋና ወጊ እንደሚኾኑ የታመነበት።

👉የፊልም ሥራቸው በሀገር ውስጥ

በፊልም በተመረቁ ዋዜማም ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ በለውጡ ማግስት በ1967 ዓ.ም በመመለስ “የ3 ሺህ ዓመት ምርት” የተሰኘውን ጥቁር እና ነጭ 16 ሚሊ ሜትር ፊልምን ቀርጸዋል።

👉ዓለማቀፍ ዕውቅና

ዛሬ በዋሽግተን ዲሲ የሚገኘው ሀዋርድ ዪኒቨርሲቲ፣ የሎሳንጀለስ ዩኒቨርሲቲ፣ ኒዎርክ የሚገኘው ዘ ሴንተር ፎር ሂውማን ራይት ኤንድ ዘአርት አት ባርድ ኮሌጅ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የፊልም ተቋማት “የ3 ሺህ ዓመት ምርት” ፊልምን የአፍሪካ ታሪክ፣ ማኅበራዊ ፍትሕ፣ አፍሪካ ድህረ ቅኝ ግዛት እንዲሁም ገለልተኛ ፊልም ሰሪ በሚል ለማስተማሪያ ይጠቀሙበታል።

ከ1975 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ በፊልም ፕሮፌሰርነት ለረጅም ዓመታት በማስተማር ብዙ ጥቁር የፊልም ደረሲያንን ኮትኩተው አሳድገዋል።

በገለልተኛ ፊልም ሥራዎች አንቱ በመባል በጥቁሮች የሲኒማ ታሪክ ከፍተኛ ማማ ላይ መድረስም ችለዋል።

ሎሳጅለስ ካሊፎርኒያ የሚገኘው “ዘ አካዳሚ ሙዝየም ኦፍ ሞሺን ፒክቸርስ” የቫንቴጅ ሽልማት የመጀመሪያው ተሸላሚ ኢትዮጵያዊም ናቸው ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ።

ሙዝየሙ በሲኒማ ዙሪያ ዋነኛ ትርክቶችን በመገዳደር እና አውድ በማስያዝ የረዳ አርቲስት እና ምሁር በሚል ማዕረግ ሰጥቶም አክብሯቸዋል።

👉ኢትጵያዊ እና አፍሪካዊ እሳቤያቸው

ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ በሠሯቸው ሥራዎች እና በሕይዎታቻው ሁሉ ኢትዮጵያ ከልባቸው እና ከአፋቸው አትጠፋም።

“ታሪኩን የማያከብር ትውልድ መቼም ታሪክ አይሠራም፤ እንደ ዓመድ ክምር በኖ እና ተበትኖ ይጠፋል እንጅ” በሚል ንግግራቸውም ይታወቃሉ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ።

የፊልም ሥራዎቻቸው በኢትዮጵያዊ ማንነታቸው ላይ የተመሠረተ ቢኾንም ከምንም እና ማንም በላይ በሰፊው የፓን አፍሪካን ራዕይን የሚያስተጋቡ ሰውም ናቸው።

የፊልም ሚዲያን ለነጻነት መታገያ እና ፍትሕ ለተጓደለባቸው መሳሪያነት የሚጠቀሙ ታዋቂ አፍሪካዊ ምሁር እና የሲኒማ ተራኪም በመኾን ክብር ያላቸው ሰውም ናቸው።

ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ በአበረከቷቸው አስደናቂ የሲኒማ ሥራዎቻቸውም ኾነ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ኢትዮጵያዊነትን በማስተዋወቅ አቻ የማይገኝላቸው ሲኾኑ አፍሪካዊነትንም ከፍ አድርገው የሚያቀነቅኑ ምርጥ አፍሪካዊ ምሁርም ጭምር ናቸው፡፡

ሥራዎቻቸውም በአብዛኛው የተጨቆኑ እና የተገለሉ ሕዝቦችን ሕይዎት ያማከሉ፤ ተቃውሞን፣ ነፃነትን እና ፍትሕን የሚያበረታቱ ናቸው።

ሥርዓታዊ ዘረኝነትን በማጋለጥ እና በእኩልነት ላይ ያለማመንታት ጥብቅና በመቆም ታዋቂ ዓለም አቀፍ ድምጽ መኾንም ችለዋል።

በጥቁር ሕዝቦች ላይ የተፈጸሙ ግፎችን፥ ጭቆናን እና ዘረኝነትን ሳይታክቱ ያወገዙ እና ለዕኩልነት የሚታገሉ ዓለም አቀፋዊ የጥበብ ሰው ናቸው።

የፕሮፌሰር ኃይሌ ሥራዎች በተደጋጋሚ በምዕራባዊያን የፊልም ኢንዱስትሪ አጋፋሪዎች የተገለሉበት ምክንያት በድፍረት ዕውነትን፣ ፍትሕ እና የሰብዓዊ እኩልነትን በመሥበክ የዓለም አቀፍ ድምጽ በመኾናቸው ነው።

👉ከታዋቂ የፊልም ሥራዎቻቸው መካከልም በጥቂቱ ለመጥቀስ ፦

✍️ አድዋ — የአፍሪካ ድል ( Adwa: An African Victory)

✍️ ሳንኮፋ — ስለ ዝርያዊ ባርነት፣ የአፍሪካ ማንናት እና የባሕላዊ ነፃነት።

✍️ ጤዛ — ስለ ስደት እና የፖለቲካ ትግል ይጠቀሳሉ።

እነዚህ ፊልሞች ከመዝናኛ ባለፈ የአፍሪካ ጽናት እና ባሕልን አጉልተው የሚያሳዩም ናቸው።

አሁን ላይ እነዚህን እና ሌሎች በርካታ አበረከቷቸውን ለመዘከር ብሎም ትውልድ እንዲማርባቸው ለማድረግ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሴኔት ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም በማራኪ ግቢ የሚገኘውን የፊልም ትምህርት ክፍል አዳራሽ “ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ሲኒማ አዳራሽ” ብሎ በመሰየም ከፍተኛውን የክብር ምልክት ሰጥቷቸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየመሬት መንሸራተት እና የጎርፍ አደጋን ለመቀነስ ሁሉም ርብርብ ማድረግ አለበት።
Next articleየጎንደር ከተማ ማኅበረሰቡን በቅንነት እና በታማኝነት ላገለገሉ ተቋማት እና ባለሙያዎች ዕውቅና ሰጠ።