
ደብረ ማርቆስ: ነሐሴ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ ጎጃም ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት በሴፍቲኔት በታቀፉ ሰባት ወረዳዎች አደጋ ሊቀንሱ እና ሃብት ሊፈጥሩ በሚችሉ ዘርፎች ላይ እየሠራ መኾኑን አስታውቋል ።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተሾመ መኮንን ከክልሉ በተገኘ ከ319 ሚሊዮን ብር በላይ የበጀት ድጋፍ ከ102 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ታላሚ የማኅበረሰብ ክፍሎች በቀጥታ እና በማኅበረሰብ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መኮኑን ተናግረዋል።
የአደጋ ስጋት ያለባቸውን ቀጣናዎችን በመለየት አደጋን ለመቀነስ የሚያስችሉ የችግኝ ተከላ፣ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች፣ የጎርፍ መከላከል እና እርጥበት እቀባ፣ የክትር እና የእርከን ሥራ፣ የቦይ ጠረጋ እና መሰል ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑን አብራርተዋል።
በፈተናዎች ውስጥም ኾኖ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ68 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ ለመስኖ ልማት አጋዥ የኾኑ 64 ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ እና በቀጥተኛ የገንዘብ ድጋፍ ኅብረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።
በዞኑ የዓባይ ሸለቆ አዋሳኝ የሚገኙት አዋበል፣ አነደድ፣ ደጀን፣ ሸበል በረንታ፣ እናርጅ እናውጋ እና እነብሴ ሳር ምድር ወረዳዎች ለመሬት መንሸራተት አደጋዎች ተጋላጭ መኾናቸውን ጠቁመዋል ።
በተለይ ችግሩ በተደጋጋሚ በሚከሰትባቸው ደጀን እና አዋበል ወረዳዎች ላይ በመሬት መንሸራተት ሊከሰት የሚችለውን አደጋ ለመቀነስ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች መከናወናቸውንም ተናግረዋል።
ወቅቱ ክረምት ከመኾኑ ጋር ተያይዞ ለደራሽ ጎርፍ እና ለመሬት መንሸራተት ይበልጥ ተጋላጭ በኾኑ የዓባይ ሸለቆ አዋሳኝ አካባቢዎች ኅብረተሰቡን የማንቃት ሥራ እየተከናወኑ መኾኑን ያብራሩት ኀላፊው “አደጋን ለመቀነስ ሁሉም በየደረጃው ርብርብ እንዲያደርግም” ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!