
ባሕር ዳር: ነሐሴ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የ25 ዓመታት የአሻጋሪ እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ አቅዶ ወደ ትግበራ ገብቷል። የትውልድ እና የቁጭት ዕቅዱ የአማራ ክልልን በዘላቂነት ከችግር የሚያወጣ፣ ወደ ተሻለ ዕድገት የሚያደርስ እንደኾነ ተገልጿል።
የአማራ ክልል ፕላን እና ልማት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙዩኒኬሽን ኀላፊ ሞገስ አያሌው ከአሚኮ ጋር ባደረጉት ቆይታ የ25 ዓመታት አሻጋሪ እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ የክልሉን ኢኮኖሚ በፍጥነት አረጋግቶ እንዲያገግም የሚያደርግ ነው ብለዋል። ከዚህ ባሻገር ክልሉን ወደ አዲስ ምዕራፍ እንዲመነጠቅ ማድረግ የሚያስችል መኾኑን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል የ25 ዓመታት አሻጋሪ እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ ሳይንሳዊ ዘዴን ተከትሎ የክልሉን ሕዝብ ችግሮች ለይቶ ለችግሮቹ መፍትሔ የሚኾኑ እና ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ መንገዶችን በመለየት መታቀዱን ነው የተናገሩት።
ከ25 ዓመታቱ የአሻጋሪ እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ የተቀዳ ከ2018 እስከ 2022 ዓ.ም ድረስ ተግባራዊ የሚኾን የአምስት ዓመታት ስትራቴጂክ እቅድ መታቀዱንም ገልጸዋል።
የዕቅዱ መዳረሻ ርዕይ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ አቅም መፍጠር እና ሁለንተናዊ ብልጽግና ማረጋገጥ እንደኾነ አንስተዋል። ዋነኛ አላማው እቅዱን በአግባቡ በመተግበር ክልሉን ከድህነት ማላቀቅ ብቻ ሳይኾን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲኾን ማስቻል ነው ብለዋል።
ዕቅዱን ውጤታማ ለማድረግ የትናንት ችግሮችን፣ የዛሬ አሁናዊ ሁኔታዎችን፣ የነገ ተስፋ እና ስጋቶችን ሳይንሳዊ በኾነ ትንታኔ በመለየት ማስቀመጡንም አስታውቀዋል።
ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የሕልውና ጉዳይ መኾኑን ተረድቶ ርብርብ በማድረግ እቅዱን በመፈጸም ድህነትን ታሪክ ማድረግ ይኖርበታል ነው ያሉት።
ዕቅዱ አምስቱን የኢኮኖሚ ምሰሶዎች ለይቶ ማስቀመጡን የተናገሩት ኀላፊው በዕቅዱ ከተለዩት ዘርፎች አንዱ የግብርናው ዘርፍ መኾኑን ገልጸዋል።
የግብርና ዘርፉ ለበርካታ ዜጎች የኑሮ መሰረት ከመኾኑም በተጨማሪ በክልሉም ኾነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ፣ለኢንዱስትሪ ግብዓት እና ለዋጋ ማረጋጋት ያለው ድርሻ ከፍተኛ መኾኑ ታሳቢ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
ሰፊ የዘመናዊ ግብርና መሰረት ለኢንዱስትሪ መነሻ አቅም ነው ያሉት ኀላፊው ግብርናውን ለማዘመን የሚረዱ ሥራዎች በትኩረት እንደሚሠራባቸው ገልጸዋል።
የነበሩትን አዝጋሚ መዋቅራዊ ለውጦችን፣ ዝቅተኛ የግብርና አቅሞችን፣ የዕውቀት፣ የክህሎት እና የአመለካከት ችግሮችን በመቅረፍ ጥምር የግብርና አቅሞችን፣ የማጎልበት፣ የመስኖ፣ የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂን በመጠቀም በትኩረት መሠራት ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
ለበርካታ የክልሉ ማኅበረሰብ የኑሮ መሰረት የኾነውን ግብርና በማዘመን የገጠር ድህነትን ማጥፋት ይገባል ብለዋል።
የተሻሻለ መኖ፣ የተሻሻለ ዝርያ እና የእንስሳት ሕክምና በመጠቀም የእንስሳት ሀብት ልማትን ማሳደግ፣ የእንስሳት ፋይዳን ከግብዓትነት እና ጥሪትነት ወደ እሴት በመቀየር ምርታማነት እና ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ባላቸው የግብርና ምርቶች ላይ አተኩሮ በመሥራት ለውጤታማነቱ ጥረት መደረግ ይኖርበታልም ብለዋል፡፡
የአምራች ኢንዱስትሪውን የጥሬ ዕቃ ፍላጎት የማሟላት፣ እያደገ የሚመጣውን የከተሜ የምግብ ፍላጎት የማሟላት እና በዓለም ላይ እየጨመረ የሚመጣውን የምግብ ፍላጎት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የክልሉን እና የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት የመደገፍ ሚናን ማሳደግ ትኩረት እንደሚደረግበት ገልጸዋል።
ይህን ውጤታማ ለማድረግ ለዘመናዊ ግብርና የሚመጥን የሠለጠነ የሰው ኀይል መፍጠርም ይኖርብናል ነው ያሉት።
የአሻጋሪ እድገት እና ዘላቂ ልማት ዕቅዱን በተሳካ ሁኔታ መፈጸም ከተቻለ ክልሉ አሁን ካለበት የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮች ተላቆ ወደ ብልጽግና መሸጋገር ይቻላል ብለዋል።
እቅዱ እስካሁን በክልልም ኾነ በሀገር ደረጃ በአይነቱ ልዩ የኾነ እና ሳይንሳዊ መንገድን ተከትሎ የተዘጋጀ መኾኑንም አንስተዋል።
እቅዱ ስኬታማ እንዲኾን ለክልሉ እና ለሀገር እድገት የተጉ እጆች እና ቅን ልቦች ሊኖሩ እንደሚገባም አመላክተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን