አሚኮ ለቋንቋ እና ባሕል እድገት ተግቶ የሚሠራ ሚዲያ ነው።

13

ሰቆጣ: ነሐሴ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ በትንሽ ቤት እና በውስን ሰዓት የጀመረውን የስርጭት አድማስ አስፍቶ ዛሬ ላይ በሁለት የቴሌቭዥን ማሰራጫ ቻናል እና በ12 ቋንቋዎች ለማኅበረሰቡ መረጃዎችን በትጋት እያደረሰ ያለ የሕዝብ ሃብት ነው።

የጎልማሳ ዕድሜን ያስቆጠረው አሚኮ በየጊዜው ከፍታን እያሳየ እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን እየተቀዳጀ እነኾ 30ኛ ዓመቱን በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ ይገኛል።

ይህንን በማስመልከትም የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንታይቱ ካሴ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። አሚኮ የአማራ ክልል ሃብት ብቻ ሳይኾን የመላው ኢትዮጵያውያን ሃብት ነው ብለዋል።

አሚኮ ለብሔረሰብ አሥተዳደሩ ቋንቋ እድገት ያበረከተው አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም ያሉት አፈ ጉባኤዋ የዋግ ኽምራን መገለጫ ሻደይን በማስተዋወቅ እና የምክር ቤቱን አጀንዳዎች በመከታተል ለሕዝብ ጆሮ እያደረሰ ያለ ትልቅ ሚዲያ እንደኾነ ነው የገለጹት።

የዋግ ኽምራ ጸጋዎች፣ ሃብቶች እና የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች በሁሉም የዜና አውታሮቹ ከመዘገብ ባሻገር በዶክመንተሪ ፊልም እያዘጋጀ ለትውልድ እንዲተላለፍ አድርጓል ነው ያሉት። በቀጣይም ይበልጥ አሻሽሎ ሊያስቀጥል እንደሚገባም አንስተዋል።

ለብሔረሰብ ቋንቋው እድገት አበክሮ እየሠራ ያለው ተቋሙ በሰቆጣ ከተማ ያስገነባውን የኤፍ ኤም ማሰራጫ ግንባታ አስፈላጊውን ግብዓት በማሟላት በቅርብ ወደ ሥርጭት እንዲገባም ጠይቀዋል። የኤፍ ኤም ጣቢያው መጀመር ለዋግ ሕዝብ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ እንደኾነም ተናግረዋል።

ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለትምህርት ጥራት እና ለትምህርት ቤቶች ገጽታ መለወጥ አሚኮ ባለፉት 30 ዓመታት የማይተካ ሚና ተጫውቷል።
Next articleየአሻጋሪ እና የዘላቂ ልማት ዕቅዱ ክልሉ ወደ አዲስ ምዕራፍ እንዲመነጠቅ የሚያደርግ ነው።