ኮረማሽ የዓፄ ምኒልክ የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤት፡፡

788

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 30/2012 ዓ.ም (አብመድ) ኮርማሽ የዳግማዊ ዓጼ ምኒልክ የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤት ነው፤ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በሀገረማርያም ከሰም ወረዳ ኮረማሽ ከተማ ይገኛል፡፡ ከአዲስ አበባ ወደ ደብረ ብርሃን አቅጣጫ በ88 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡

የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤቱ 15 ሺህ 595 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈና የዙሪያ ርዝመቱ 532 ነጥብ 3 ሜትር የሆነ ግቢ ነው፡፡

የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤቱ በግቢው ውስጥ የጥንት ይዞታቸውን የጠበቁ ሰባት ቤቶች አሁንም ድረስ ይገኛሉ፡፡ በቅርብ የተሠሩ ሦስት ቤቶችም ከዚያው ሰፊ ግቢ ውስጥ አሉ፡፡ ግቢው በፅድ ዛፎች የተዋበ ነው፡፡ የአብመድ የጋዜጠኞች ቡድን ወደ ሰሜን ሸዋ ዞን ሀገረማሪያም ከሰም ወረዳ ተጉዞ የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤቱን ተመልክቷል፡፡

የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤቱ የተመሠረተው በ189ዐ ዓ.ም መሆኑን የሚናገር ገና መግቢያ በሩ ላይ የተለጠፈ ጽሑፍ አለ፡፡ የሀገረማሪያም ከሰም ወረዳ ባህል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ቅርስ ጥበቃ እና ፕሮሞሽን ቡድን መሪ አቶ ደስታ ታደሰ እንዳብራሩት ለጦር መሳሪያ ግምጃ ቤቱ ዋነኛ መመሥረት ምክንያት የዓድዋ ጦርነት ነው፡፡

ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ የዓድዋን ጦርነት ድል ካደረጉ በኋላ ጠላት ዳግመኛ ቢመጣ የሚመክቱበት ጦር መሣሪያ ማከማቻ የሚሆን፣ ጠላት በቀላሉ የማይደርስበት ስትራቴጂካዊ ቦታ እንደሚያስፈልጋቸው ያስቡ ነበር፡፡ ለዚህም ሹማምንቱን ያማክሩ ነበር፡፡ በተለይም የቡልጋው ገዥ ራስ ዳርጌ ሳኅለሥላሴም ከግዛታቸው ምቹ የሆነ ቦታ እንዳለ አሳወቋቸው፤ ንጉሡም በተሰጣቸው ጥቆማ መሠረት ቦታውን ሄደው ዓይተው ተስማሚ መሆኑን አረጋገጡ፡፡ እስከዚያም ጊዜ ይህን ስትራቴጂክ ቦታ ባለማየታቸው ተገርመው “ሳላይሽ” ብለው ስም እንዳወጡለት ታሪክ ይናገራል፡፡ እስከ አሁንም የቦታውና የከተማው ስያሜ “ሳላይሽ” በመባል ይታወቃል፡፡

ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ቦታውን ካዩበት ጊዜ አንስተው የመገንቢያ ቁሳቁስ ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ ሀገር ድረስ አሰባስበዋል፡፡ ቤቱ የተሠራው ከጭቃ፣ ድንጋይ፣ እንጨት እና ቆርቆሮ ነው፡፡ ለፎቅ ቤቱ ርብራብ እንጨት በሰው ኃይል ቀረበ፤ ቆርቆሮ እና ሚስማር ከፈረንሳይ እስከ ጅቡቲ ከዚያም እስከ ኮረማሽ (የጦር ግምጃ ቤቱ እስካለበት) ደግሞ በ500 ግመሎች ተጓጓዘ፡፡ ቤቶቹ 16 ሜትር በ8 ሜትር የወለል ስፋት እና አራት ሜትር ከፍታ አላቸው፡፡ የምድር ቤትና ፎቅ ናቸው፡፡ በውስጣቸውም በድንጋይ የተገነቡ ሁለት ሁለት እንደ ምሰሶ የሚያገለግሉ የፎቁ ርብራብ ያረፈባቸው ግርግዳዎች ይታያሉ፡፡

የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤቱ በተሠራ ጊዜም የንጉሡ ታማኝና ታዛዥ አገልጋዮች ከ14ቱም ክፍላተ ሀገራት በአንድ ጋሻ መሬት ክፍያ እንደመጡ ታሪክ ያወሳል፡፡ ግምጃ ቤቱ ተሠርቶ ከተጠናቀቀ በኋላ የዲኘሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን በመቀጠል ከፈረንሳይ ሀገር የጦር መሣሪያ በማምጣት እንዳከማቹበት መረጃዎች ይገልፃሉ፡፡

ግምጃ ቤቱ ተገንብቶ በ189ዐ ዓ.ም ተጠናቀቀ፤ መሣሪያው ተጓጉዞ ሥፍራው ከደረሰ ሁለት ዓመታት ጀምሮ ለ36 ዓመታት በጦር መሣሪያ ግምጃ ቤትነት አገልግሏል፡፡ በ1928 ዓ.ም ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜም በግምጃ ቤቱ የነበሩ የጦር መሳሪያ ወደ በአካባቢው አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኝ ኮረማሽ ዋሻ እንደተወሰደና ቀሪውንም ለአርበኞች መዋጊያ እንደተከፋፈለ ይነገራል፡፡ ወራሪው ኃይልም በግምጃ ቤቱ የጦር መሣሪያ እንዳላገኘ ይነገራል፡፡ ወራሪው የጣሊያን ጦር ከሀገር ከተባረረ በኋላም እስከ 1954 ዓ.ም ድረስ በጦር ካምፕነት ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ የጦር ካምፑ ወደ አሌልቱ ሲዛወር የቡልጋ ገዥዎች መቀመጫ በመሆን አገልግሏል፤ በደርግ መንግሥትም የሕዝብ መሰብሰቢያ አዳራሽና ለተለያዩ የቢሮ አገልግሎቶች እንደዋለ ከቡድን መሪው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ይህ ታሪካዊ ቅርስ በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ምክንያቶች የመፈራረስ አደጋ ገጥሞት ነበር፤ የወረዳው ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ባደረገው ጥረት ከፌዴራል ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን 30 ሺህ ብር፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 30 ሺህ ብር በተገኘ ድጋፍ ጥገና ተደርጎለታል፡፡ በግቢው ውስጥ የተወሰኑ የወረዳ አስተዳደሩ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ይገለገሉበት እንደነበር እና ለቅርሱ ደኅንነት ሲባል ከመስከረም 2ዐዐ4 ዓ.ም ጀምሮ ግቢውን ለቅቀው እንዲወጡ እንደተደረገ አቶ ደስታ ታደሰ ተናግረዋል፡፡
ግቢው ጥበቃና አትክልተኛ ተቀጥሮለት እንክብካቤ እየተደረገለት ነው፡፡ ለጎብኚዎች ክፍት ተደርጎ ገቢ እንዲያመነጭም ተደርጓል፡፡ የጦር ግምጃ ቤቱ ግቢ ዙሪያ የአካባቢው አስደናቂ መልክአ ምድርም ተጨማሪ የጎብኚዎች መዳረሻ ነው፡፡

የጦር ግምጃ ቤቱ ከወረዳው ዋና ከተማ ራቅ ብሎ በመገኘቱ ወጣቶች በዘርፉ ወደ ሥራ ለመሰማራት ፍላጎታቸው አነሰተኛ መሆኑን አቶ ደስታ ታደሰ ተናግረዋል፡፡ ለቅርሱ ለጥንቃቄ ሲባልም በውስጡ ባለሀብቶችን ማሰማራት እንዳልተፈለገ አብራርተዋል፡፡ በተያዘው 2012 ዓ.ም 547 የሀገር ውስጥ እና 26 የውጭ ሀገር ቱሪስቶች የጦር ግምጃ ቤቱን ጎብኝተው 12 ሺህ 240 ብር ገቢ መገኘቱንም አስረድተዋል፡፡

የኮረማሽ ከተማ ነዋሪው አባ ዳዊት ወልደገብረኤል የጦር ግምጃ ቤቱ ለአካባቢው ነዋሪ የጀግንነት ተምሳሌት ተደርጎ የሚወሰድ ቅርስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የወረዳው አስተዳደር ከ2ዐዐ5 ዓ.ም ጀምሮ ግቢውን እየተንከባከበ መሆኑንም አድንቀዋል፡፡ እርሳችውም የጦር ግምጃ ቤቱን ለመጎብኘት ወደ ሥፍራው ለሚመጡ እንግዶች የሚመጥን አቀባበል እንደሚያደርጉና ታሪኩን እንደሚያስረዱም ተናግረዋል፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰብም ቅርሱን በባለቤትነት እየተንከባከበና እየጠበቀ መሆኑን አባ ዳዊት ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከወረዳው ባህል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ተጠቀመናል

Previous articleበኢትዮጵያ ተጨማሪ 86 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኘባቸው፤ ሰባት ተጨማሪ ሰዎች ሕይወትም አልፏል፡፡
Next articleኢትዮጵያ ዕድገት የምታመጣው የኃይል ማመንጫና የመስኖ ግድቦቿን ቁጥር ስታሳድግ መሆኑን ምሁራን አስገነዘቡ።