
ጎንደር: ነሐሴ 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ “ኢንቨስትመንት ለሰላም ሰላም ለኢንቨስትመንት” በሚል መሪ መልዕክት የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2018 ዕቅድ ትውውቅ መርሐ ግብርን አካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ጎንደር እና አካባቢው የቅባት እህል፣ ቅመማ ቅመም፣ የበርካታ ቅርስ መገኛ፣ በግብርና እና በአምራች ዘርፍ ያልተነካ ሃብት ያለበት አካባቢ ነው ያሉት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ግርማይ ልጃለም ናቸው። መንግሥት እና ባለሃብቶች በጋራ በመኾን የተለያዩ ዘርፎች ላይ የልማት ሥራዎችን እያከናወኑ መኾኑን መምሪያ ኀላፊው አንስተዋል። ለአብነትም የጎርጎራ ፕሮጀክት፣ የፋሲል አብያተ መንግሥታት ዕድሳት፣ የመገጭ ግድብ እና የኮሪደር ልማት ሥራዎች ትልቅ ሃብት ፈሰስ የተደረገባቸው እንደኾኑም ጠቅሰዋል።
በ2017 በጀት ዓመት ለ283 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ የተሰጠበት ዓመት እንደነበር ገልጸዋል። ሦስት ቢሊዩን ብር ብድር የቀረበበት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ እና ተኪ ምርት በማምረት ውጤት የተገኘበት ስኬታማ ዓመት እንደነበርም አብራርተዋል።የኢንቨስትመንት ቦታ ወስደው ያላለሙ 34 ባለሃብቶችን የቦታ መንጠቅ እና ማስጠንቀቂያ የመስጠት ሥራ እንደተከናወነም ተናግረዋል። የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ሰላም እና ኢንቨስትመንት የማይነጣጠሉ ተግባራት በመኾናቸው ሰላምን መጠበቅ እና ጎንደርን ማልማት ከሁሉም የሚጠበቅ ኀላፊነት ነው ብለዋል።
ብለሹ አሠራርን በማስወገድ ባለሃብቶችን የመሳብ ሥራ መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል። ባለሃብቶች በጎንደር ከተማ እንዲያለሙ ብድር ከሚያቀርቡ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሠራ እንደኾነ ነው የገለጹት። የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጎንደር ዲስትሪክት ሥራ አሥኪያጅ እሱባለው ሰቦቃ በ2017 በጀት ዓመት በከተማው ለሚያለሙ ባለሃብቶች 540 ሚሊዮን ብር ብድር ማቅረባቸውን ተናግረዋል። በበጀት ዓመቱ ብድር የቀረበላቸው ስድስት ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ መግባታቸውንም ገልጸዋል። በቀጣይም በከተማው የሚደረገውን ኢንቨስትመንት ለመደገፍ እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።
በውይይቱ ተሳታፊ ከኾኑ አልሚዎች መካከል የዞብል ቆርቆሮ ፋብሪካ ምክትል ሥራ አሥኪያጅ ዮሐንስ መላኩ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ከቀረጥ ነጻ ግብዓቶችን እና የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ድጋፎችን እያደረገላቸው መኾኑን ተናግረዋል። አሁንም ኢንቨስትመንቱን ለማበረታታት የሚያስፈልጉ ድጋፎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ጠይቀዋል።
ዘጋቢ- ዳንኤል ወርቄ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!