ተስፋ ሰጨው የወተት ልማት

24
ባሕር ዳር: ነሐሴ 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አንድ ሰው በዓመት ከ175 እስከ 200 ሊትር ወተት መጠቀም እንዳለበት የዓለም ጤና ድርጅት፣ የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት ቢያስቀምጡም የኢትዮጵያውያን አማካይ ዓመታዊ የወተት ፍጆታ ግን 20 ሊትር እንኳ አይደርስም። በኢትዮጵያ የወተት ምርት ከተጠቃሚዎች ፍላጎት አንፃር በየዓመቱ ከ22 ቢሊዮን ሊትር በላይ ቢያስፈልግም በአሁኑ ወቅት የሚመረተው ግን ከ7 ነጥብ 1 ቢሊዮን በላይ ሊትር አይበልጥም።
ፍላጎቱን ለማሟላት ደግሞ ኢትዮጵያ የወተት ተዋጽኦዎችን ከውጭ ስታስገባ ቆይታለች። የአማራ ክልል እንስሳት እና አሳ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት መረጃ እንደሚያሳየው በክልሉ 20 ሚሊዮን የሚጠጋ የዳልጋ ከብት እንዳለው ቢገመትም ክልሉ ካለው ሀብት አኳያ የሚጠበቀውን ያህል ምርት እየተገኘ አይደለም። ክልሉ ካለው ሀብት አኳያ የእንስሳት በተለይም ደግሞ የወተት ምርታማነትን ለማሳደግ የተሻሻሉ የወተት ላሞችን የማዳቀል እና ወጣቶችን በዘርፉ የማሠማራት ሥራ እየተሠራ ይገኛል።
በተሻሻሉ የወተት ላሞች ርባታ ከተሠማሩት ወጣቶች መካከል በረከት እና የምሥራች ማኅበር ይገኝበታል። የማኅበሩ ሥራ አሥኪያጅ ሙላት ካሳው እንዳሉት ወደ ሥራው ከመግባታቸው በፊት በተለያዩ ሥራዎች ተሠማርተው ቆይተዋል። ይሁን እንጅ የሥራ አዋጭነት ጥናት በማካሄድ ከሦስት ዓመታት በፊት በሁለት የተሻሻሉ ላሞች ወደ ርባታ ገብተዋል። ወተት እና የወተት ተዋጽኦዎችንም ለማኅበረሰቡ እያቀረቡ ይገኛሉ።በሁለት ከብቶች እርባታ የተጀመረው ሥራ አሁን ላይ ከቋሚ ሀብት ውጭ ከ30 በላይ የተሻሻሉ እንስሳት እያረቡ ይገኛሉ። በዚህም በባሕር ዳር ከተማ አራት ቦታዎች ወተት፣ እርጎ፣ አይቭ፣ ሞዘሬላ፣ ቅቤ፣ አሳ እና እንቁላል በማቅረቡ ገበያውን በማረጋጋት የድርሻቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።
ወተት ብቻ በቀን እስከ 98 ሊትር ያቀርባሉ። ማኅበሩ ከሚያመርተው ወተት ባለፈ ከሌሎች አካባቢዎች በመረከብ ለማኅበረሰቡ እንደሚያቀርቡም ነው የገለጹት።አሁን ላይ ከራሳቸው ባለፈ ለስምንት ሰዎች የሥራ እድል መፍጠር ችለዋል። ዘርፉ በትንሽ ቦታ ውጤታማ ሥራ መሥራት የሚቻልበት በመኾኑ ወጣቱን በማደራጀት ወደ ሥራ ማስገባት እንደሚገባ መክረዋል።
የአማራ ክልል እንስሳት እና አሳ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት የእንስሳት ርባታ ተዋጽኦ እና መኖ ልማት ዳይሬክተር መኳንንት ዳምጤ እንዳሉት የአማራ ክልል የእንስሳት ሃብት ከሀገሪቱ እንስሳት ሀብት 30 በመቶ ድርሻውን ይይዛል። ዳይሬክተሩ እንዳሉት ክልሉ የተለያየ አግሮ ኢኮሎጅ የያዘ፣ ከፍተኛ የገጸ እና ከርሰ ምድር የውኃ ሃብት ባለቤት፣ ለመኖ የሚውል የሰብል ተረፈ ምርት የሚገኝበት እና ከ1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የግጦሽ መሬት ባለቤት ነው።
የእንስሳት ምርታማነትን ለማሳደግ ክልሉ ያለውን አቅም መሠረት ያደረገ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። እየተሠሩ ከሚገኙ ሥራዎች ውስጥ የመኖ ልማትን በጥራት እና በብዛት ማምረት አንዱ ነው። የግጦሽ መሬቶችን በመከለል እና በመጤ አረም የተሸፈኑትን ጭምር በማስወገድ በተሻሻለ መኖ የመሸፈን ሥራ እየተሠራ መኾኑን ነው የገለጹት። አርሶ አደሮችም ባላቸው መሬት የተሻሻለ መኖ እንዲያለሙ እየተሠራ ነው ብለዋል። ከዚህም ባለፈ በክልሉ በሚገኙ 35 የመኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች የተመጣጠነ መኖ እየተመረተ ነው። 92 ሺህ ቶን የሚኾን የተመጣጠነ መኖ ለእንስሳት አርቢዎች መሠራጨቱን ለአብነት አንስተዋል።
የእንስሳት ምርትን ለማሳደግ ትኩረት የተሠጠው ሌላኛው ጉዳይ የእንስሳት ጤና ማሻሻል ነው። ለዚህ ደግሞ በየቀበሌው የሰለጠኑ ባለሙያዎች ተመድበው እየሠሩ ይገኛሉ ብለዋል። የተዘዋዋሪ በጀት በመመደብ መድኃኒት እና ክትባት በማቅረብ የቅድመ መከላከል ሥራ እየተሠራ ነው።
የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ሥራም ሌላኛው ትኩረት ነው። ለዚህ ደግሞ 560 የሚኾኑ አዳቃይ ቴክኒሻን ተመድበው ባለፈው ዓመት 261 ሺህ ላሞችን ማዳቀል ተችሏል። 144 ሺህ ጥጃዎች ደግሞ እንዲወለዱ ተደርጓል። በ2018 በጀት ዓመት 460 ሺህ ላሞችን በማዳቀል 200 ሺህ ጥጃዎችን በማስወለድ የወተት እና የሥጋ ምርቱን ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑን ገልጸውልናል።
በ2017 በጀት ዓመት በተሠራው ሥራ ከአንድ የአካባቢ ላም አማካይ ይገኝ የነበረውን አንድ ሊትር ወተት ወደ ሁለት ሊትር እንዲያድግ ተደርጓል። ከተሻሻሉ ላሞች ደግሞ በአማካይ 11 ነጥብ 5 ሊትር ማግኘት ተችሏል። እንደ ደብረ ብርሃን፣ ኮምቦልቻ፣ ደሴ፣ ጎንደር ባሕር ዳር፣ ሐይቅ በመሳሰሉ ከተሞች ከ30 እስከ 45 ሊትር የሚሰጡ ላሞች ማግኘት መቻሉን ገልጸዋል። በክልሉ በተሠራው ሥራ ከአንድ ላም በአማካይ 3 ነጥብ 8 ሊትር ወተት መጨመር ተችሏል። በ2017 በጀት ዓመት በክልሉ 2 ነጥብ 16 ሚሊዮን ቶን ወተት መመረቱን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ባለፈው በጀት ዓመት 106 ሺህ የሚኾኑ ወጣቶች በእንስሳት ዘርፍ ሥራ እንዲሠማሩ ተደርጓል።
ዘጋቢ:- ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous article12ኛው የአፍሪካ ፓለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ በጋና አክራ መካሄድ ጀመረ።
Next articleሰላም እና ኢንቨስትመንት የማይነጣጠሉ ተግባራት ናቸው።