“ወፌ ሰንብታ ሰንብታ መጣች ለፍልሰታ”

73
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሚጾሙ አጽዋማት መካከል ፍልሰታ አንደኛዋ ናት። ጾመ ፍልሰታ ለብዙዎች የልጅነት ትውስታ ናት።
ጾመ ፍልሰታ ስትታሰብ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሃይማኖት ሥር ያደገ ሁሉ የልጅነት ዘመኑን ማስታወሱ የሚቀር አይመስልም። ያም የልጅነት ጊዜ ተናፋቂ ነው። ፍልሰታ በመጣች ቁጥር የልጅነት ዘመኔን አስታውሳለሁ። ያን የማይረሳ ጊዜም እናፍቃለሁ። የእኔ ልጅነት ጊዜዬ እና የፍልሰታ ትዝታዬ ከባሕር ዳር ፈለገ ነነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ውስጥ ነው። በዚህ ቤተክርስቲያን ውስጥ የነሐሴ ወር መጀመሪያ ልዩ ጊዜ ነው።
ልጆች ከወላጆቻችን ጋር ይጾማሉ። በአባቶች እግር ሥር ተቀምጠው ይማራሉ። እኔም እንዲህ ነበር ያደኩት። በጾመ ፍልሰታ የምንማረው ሃይማኖታዊ እና ግብረገባዊ ትምህርት ዛሬም ከትዝታየ ማኅደር አልወጣም። ይህ ጊዜ አሁን ላለሁበት መሠረቴ ነው። የሕጻናት መዝሙር፣ የሰንበት ትምህርቱ፣ የጣኑ ሽታ እና ሥርዓተ ቅዳሴው ሁሉም የማይረሳ ትዝታ ነው።
በተለይም ከቁርባን በኋላ ከ’እማ ሀብትሽ’ እጅ የምናገኘው ልዩ ጉርሻ አሁንም ድረስ ይታወሰኛል። እማ ሃብትሽ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን በር ላይ ተቀምጠው ቆርበው የሚወጡ ሕጻናትን የሚመግቡ እናት ናቸው። እሳቸው ሕጻናት ቆርበው ሲወጡ ምግብ ይሰጣሉ። ሕጻናቱም በደስታ ከእሳቸው እጅ ይቀበላሉ። እሳቸው በሁሉም ሕጻናት የሚወደዱ እናት ነበሩ። ከእሳቸው ምግብ ከቀመስን በኋላ ነበር ቤተሰቦቻችን የያዙልንን ምግብ የምንመገበው።
በዚያ የልጅነት ዘመን ሕጻናት በአንድ ላይ ኾነን እንዲህ እንዘምር ነበር።
ወፌ ሰንብታ ሰንብታ
መጣች ለፍልሰታ(2)
ሀገርሽ የት ነው ኤፍራታ
አሳድሪኝ ማታ
በክንፍሽ ጥላ ጋርደሽኝ
ከልጅሽ ስፍራ ወስደሽኝ
እንዳልቆምብሽ በግራ
እንዳያሰቃየኝ መከራ
ወፌ ነፍሴን አደራ።
እያልን እንዘምር ነበር። እነኚህ ስንኞች ጸሎት እና ልመናም ናቸው። በልጅነት አንድበት እና በልጅነት ልቡና ለቅድስት ድንግል ማርያም የሚሠጡ የአደራ ቃልም ናቸው።
በፍልሰታ ወላጆች ለልጆቻቸው የሚሰጧቸው እንክብካቤ የተለየ ነው ፤ በተለይም ከቁርባን መልበስ ልጆች አይገረፉም፣ ቆሻሻ አይነኩም። ያቺ ጊዜ ለሕጻናት ልዩ ሥፍራ አላት። እና ጾመ ፍልሰታን ይናፍቋታል። ዓመት ደርሶ እስክትመጣ ድረስ በጉጉት ይጠብቋታል። በቤተሰብ እና በቤተ ክርስቲያን ልዩ እንክብካቤ የሚታደግባቸው የልጅነት ጊዜያት የብዙ ሕጻናት ሕይወት መሠረት ናቸው። የመልካም ስብዕና መገንቢያ ጊዜያትም ናቸው።
ጾመ ፍልሰታ ከሌሎች አጽዋማት በተለየ መልኩ ሕጻናት በብዛት ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመጡባት፣ የሚጾሙባት እና የሚቆርቡባት ጊዜ ናት።
ዓመታት ዓመታትን ተክተው፣ የልጅነት ዘመን አልፎ፣ እኔም የልጆች እናት ኾኜ በጾመ ፍልሰታ በአደኩበት አጸድ ሥር ከልጆቼ ጋር ቆሜያለሁ። በልጆቼ አሁን እና ትናንትን ተመለከተኩ። የልጅነት ዘመኔን አስታወስኩ። ያን ተመልሶ የማይመጣ እና የሚናፈቅ የልጅነት ዘመኔን አሰብኩ፣ አንሰላሰልኩ።
በዚሁ አጸድ ሥር ከአንዲት እናት ጋር ተገናኝቻለሁ። ወይዘሮ ብርቱካን አዳሙ ይባላሉ። አራት ልጆችን አሳድገዋል። “ጾመ ፍልሰታ ልጆቻችን እምነታቸውን እያወቁ እንዲያድጉ፣ መልካም ሥነ ምግባር እንዲኖራቸው እና ፈሪሐ እግዚአብሔር እንዲያድርባቸው መሠረት የምትጥል ወቅት ናት” ይላሉ።
በጾመ ፍልሰታ ወቅት የቁርባን ሰዓት እስከሚደርስ በሰንበት ትምህርት ቤት የሚሰጠውን ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ይከታተላሉ። ይህም ጥሩ ስነ ምግባር ይዞ ለመውጣት መነሻ ይሆናቸዋል ነው የሚሉት። ታላላቆቹ ልጆቻቸው በጾመ ፍስለታ የጀመሩትን ቁርባን እና የሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት አስቀጥለው አስካሁን መያዛቸውንም ነግረውናል። በቤት ውስጥም ወላጆቻቸውን አክባሪ፣ ታዛዥ እና በጎረቤቶቻችን ዘንድም በስነ ምግባራቸው በመልካም የሚነሱ ልጆች ናቸው ይላሉ። ፍልሰታ የሕጻናት የስነ ምግባር መሠረት መጣያ እንደኾነችም አንስተዋል።
በቤት እና በጎረቤት የተጀመረች መልካምነት ደግሞ ለሀገር እና ለሕዝብ ትተርፋለች። በጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን የአራቱ ጉባኤያት ምክትል መምህር መምህር ዘላለም ሀዲስ ጾመ ፍልሰታ የልጆችን ግብረ ገብነት ለመገንባት ወሳኝ ጊዜ ናት ይላሉ። በሌሎች አጽዋማት አረጋውያን እና ካህናት በብዛት ይጾማሉ። በፍልሰታ ወቅት ግን ሕጻናትም በብዛት በቤተክርስቲያን አጸድ ሥር ተገኝተው ሥርዓቱን ይከታተላሉ። ይጾማሉ። ይጸልያሉ። በሰንበት ትምህርት ቤት ትምህርት ይማራሉ። ይህም ለሕጻናት ልዩ ትዝታ ነው።
በጾመ ፍልሰታ ሕጻናት ከሰዎች አክብሮት እስከ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ድረስ እንደሚማሩም ነግረውናል። ይህች ጾም ብዙ ሕጻናት ከልጅነታቸው ጀምሮ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርቶች በመከታተል፣ አገልግሎት በመስጠት እና በሰንበት ትምህርት ቤቶች በመሳተፍ፣ በሃይማኖታቸውና በጥሩ ሥነ ምግባር ታንጸው እንዲያድጉ ምክንያት እንደምትኾንም ገልጸዋል። የጾመ ፍልሰታ ጊዜ ለወጣቶችም የሥነ ምግባር ትምህርት የሚቀስሙበት ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚቀርቡበት እና ጸሎታቸውን ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርቡበት ወሳኝ ወቅት እንደኾነችም ነግረውናል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ይህንን ልምምድ ለዘመናት በመከወን፣ ሕጻናትን በግብረ ገብነት በመቅረጽ፣ ስለ ሃይማኖታቸው በማስተማር እና የሀገራቸውን ባሕል እና ትውፊት እንዲጠብቁ በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገች ትገኛለች ነው ያሉት። ጾመ ፍልሰታ ሃይማኖታዊ ሥርዓት የሚከውንባት ብቻ ሳትኾን የልጆችን እና የወጣቶችን ሥነ ምግባር፣ ማንነትን በመገንባት ረገድ ትልቅ ሚና የምትጫወት ናት ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየተጠባባቂ ጥሪ ማስታዎቂያ፦
Next article12ኛው የአፍሪካ ፓለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ በጋና አክራ መካሄድ ጀመረ።