ሥንቶቻችን ሥራችንን በዕቅድ እንመራ ይኾን?

14
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አንድን ሥራ ውጤታማ ለማድረግ ሰዎች የተለያዩ መንገዶችን ይጠቀማሉ። ብዙ ይለፋሉ፣ ይጥራሉም። አንዳንዶቹ በቀላሉ ሲሳኩ አንዳንዶቹ ደግሞ ረጅም ጊዜን ይወስዳሉ።
ሀገር የምትገነባው ታዲያ የእነዚህ ግለሰቦች ድምር የሥራ ትጋት በሚፈጥረው ውጤት ይኾናል። ብዙ ጊዜ የግለሰቦች የመፈጸም አቅም የሀገርን ሁለንተናዊ አቅም እንደሚወስን የሚረዳው እና በዚሁ መንገድ የሚንቀሳቀሰው ምን ያህሉ ይኾን ?
👉ግለሰባዊ ዕቅድ ምን ያክል ሥራዎች በቀላሉ እንዲሳኩ ያደርግ ይኾን?
ስቲቨን ኮቬይ የተባሉ ሰው የውጤታማ ሰዎች ሰባቱ ልምዶች (The 7 Habits of Highly Effective People) በሚል ባሳተሙት ጽሑፍ ላይ እንደሚሉት ማንኛውንም ተግባር ከመጀመርህ በፊት ግብህ እና የመጨረሻ ውጤቱ ምን መኾን እንዳለበት በግልጽ አስቀምጥ ይላሉ። ይህም በምትሠራው ሥራ ሁሉ ወደ ዋናው ግብህ እንድታመራ ይረዳሃል ነው የሚሉት። ኮቬይ ይህ መርህ የራስህ ዕጣ ፈንታ ለመወሰን ያግዝሃል ባይ ናቸው።
ጸሐፊው እንደሚሉት ግለሰቦች ውጤት ለማምጣት በዕቅድ ከመመራት ባለፈ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ቅድሚያ ሰጥተው ቢሠሩ ውጤታማ ሊኾኑ እንደሚችሉ ይመክራሉ።ሰዎች አላስፈላጊ በኾኑ ጉዳዮች ላይ ጊዜ እና ጉልበታቸውን እንደሚያባክኑ የሚናገሩት ጸሐፊው ይህም የዕቅድ አለማቀድ ክፍተት ነው ይላሉ።
ብራያን ትሬሲ የተባሉ ሌላኛው ጸሐፊ ሰዎች ዕቅድ ከሌላቸው እና ግልጽ ግቦችን አውጥተው የማይንቀሳቀሱ ከኾነ ያለ ካርታ እንደሚጓዝ መርከበኛ ነው ብለዋል። ግብን በጽሑፍ አውጥቶ በየጊዜው መከለስ አስፈላጊ መኾኑንም አመላክተዋል። ዕቅድ አቅዶ የሚንቀሳቀስ ሰው ብዙ ጊዜ ትንሽ ለፍቶ ከፍተኛ ውጤት እንዲያገኝ ያስችለዋል ነው ያሉት።
ሰዎች ግብ ላይ ለመድረስ ጥቃቅን ልማዶች ላይ ማተኮር የበለጠ ውጤታማ ሊያደርጋቸው እንደሚችል የሚያብራሩት ጸሐፊው “መጽሐፍ አንባቢ መኾን” የሚል ግብ ከማውጣት ይልቅ “በየቀኑ አምስት ገጾች ማንበብ” የሚል ልማድ መፍጠር የተሻለ ነው ባይ ናቸው። በየቀኑ በራስህ ላይ ትንሽ ለውጥ ማድረግ በዓመቱ መጨረሻ ላይ የተሻለ ሰው ለመኾን ያግዛል ነው ያሉት።
ትናንሽ ልማዶች በጊዜ ሂደት ተጠራቅመው ትልቅ ለውጥ ስለሚያመጡ ግለሰባዊ ዕቅድ ሲታቀድ ይህ መርህ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው ይገባል። ይህም ድምር ውጤቱ ሀገር ላይ የሚፈጥረው ለውጥ ትልቅ ነው ባይ ናቸው።
👉ለመኾኑ ምን ያክሎቻችን ሥራዎቻችንን በዕቅድ እንመራ ይኾን?
አሚኮ ዲጅታል ሚዲያ ያናገራቸው ግለሰቦች እንደሚሉት ሥራዎችን ባብዛኛው የሚሠሩት ሀሳቡ እንደመጣላቸው ወዲያውኑ ነው።
ስለ ዕቅድ ማቀድ ብዙም ዕውቅና እንደሌላቸው የሚናገሩት አስተያየት ሰጭዎቹ ያልተጻፈ ዕቅድ ብለው በሚጠሩት ተለምዷዊ አሠራር ሥራዎችን ይሠራሉ። ብዙ ጊዜ ዕቅድ የሚታወሰው አዲስ ዓመት ሲመጣ እንደኾነ የሚናገሩት አስተያየት ሰጭዎቹ ያለፈውና የታሰበው ሳይፈጸም ሌላ ሃሳብ በዕቅድ ደረጃ እንደሚወጥኑ ጠቅሰዋል።
አብዛኛው ያልተጻፈ የተባለው ዕቅድም ከሚፈጸመው የማይፈጸመው እንደሚበልጥ ነው ያብራሩት።
👉 ያልተጻፈ ሃሳብ ዕቅድ መባል ይችል ይኾን?
በአማራ ክልል ፕላን እና ልማት ቢሮ የማክሮ ፕላን ባለሙያ ጌትነት ወርቁ እንደሚሉት ለአንድ ግለሰብም ይሁን ሀገር ዕቅድ ወሳኝ እና አቅጣጫ ጠቋሚ ነው ይላሉ። የእያንዳንዱ ግለሰብ ዕቅድ ድምር ውጤቱ ሀገር ልትደርስበት ያሰበችውን ደረጃ የሚወስን ነው። ከሀገራዊ ዕቅዱ የተቀዳ ዕቅድ እያንዳንዱ ዜጋ ማዘጋጀት ከቻለ ውጤት በቀላሉ ማምጣት ይቻላልም ባይ ናቸው።
በተለያዩ ሥልጠናዎች ላይ ሰዎችን ሲያናግሩ አብዛኞቹ ዕቅድ አለኝ ግን ያልተጻፈ ነው ብለው ሀሳብ እንደሚሰጧቸው ባለሙያው ጠቁመዋል። ዕቅድ ተብሎ የሚጠራው ግን የተጻፈ ሲኾን ነው ብለዋል። ተሰንዶ ያልተያዘ ነገር ዕቅድ ተብሎ ሊጠራ እንደማይችል አስረድተዋል። አንድ ሰው ዕቅድ አለው የሚባለው ምን? መቼ? ለማን? እንዴት? እና መሠል ጉዳዮች የሚመልስ ሊኾን እንደሚገባም ተናግረዋል። ዕቅዱ በጊዜ የተገደበ፣ መቸ ነው የሚሠራው? ለማን ነው የምሠራው? የሚለውን ከመመለስ ባለፈ ዓላማ፣ ራዕይ እና ግብ ያለው መኾን እንዳለበትም ጠቁመዋል። ዕቅዱን ለማስፈጸምም እንደ ዕቅዱ እና የግለሰቡ አቅም በጀት ተቀምጦለት የሚፈጸም ሊኾን እንደሚገባው ነው ያስረዱት።
👉 የግለሰቦች ዕቅድ ከሀገር ዕቅድ ጋር እንዴት ይገናኛል?
አንድ ግለሰብ የሚያቅደው ዕቅድ ሁሌም ከሀገር እና ከክልሉ ዕቅድ ውጭ ሊኾን የሚችል አይደለም ያሉት ባለሙያው አንድ ሰው ለመማር ቢፈልግ ከሀገሪቱ የትምህርት ፖሊሲ እና ዕቅድ ጋር የሚገናኝ መኾኑ ተናግረዋል። ልነግድ ብሎ የተነሳ እና ያቀደ ሰውም ከሀገሪቱ ፖሊሲ እና ስትራቴጅ ጋር የሚገናኝ በመኾኑ ይህን ታሳቢ አድርጎ ማቀዱ አይቀርም ይላሉ። በግብርናም ኾነ በጤና እና በሌሎች መሠል ዘርፎች መሥራት የፈለገ ሰው በቀጥታ ከሀገሪቱ ዕቅድ ጋር መገናኘቱ አይቀርም ብለዋል። ማንኛውም ዜጋ በዕቅድ የሚመራ ከኾነ ራዕይ አለው፤ ይህ ደግሞ ነገሮች እንደፈለጉ አያወዛውዙትም፤ ያሰበበት ብቻ ለመድረስ የሚሠራ ይኾናል ነው ያሉት።
ፖለቲካውም ኾነ ኢኮኖሚው ሲዋዥቅ ሳይዋዥቁ ቀጥ ብሎ ለመመራት ዕቅዱ ወሳኝ ነው ባይ ናቸው። ዕቅድን ማቀድ የሚችል ማኅበረሰብ በመፍጠር ሀገር የምታወጣውን እና የምታወርደውን የማኅበራዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚ ተረድቶ የሚተገብር ማኅበረሰብ መፍጠር ይቻላል ይላሉ። መንግሥት የሚፈልጋቸውን እና ወደታች የሚያወርዳቸውን ዕቅዶች ተረድቶ የሚፈጽም ማኅበረሰብ ለመፍጠር ጥሩ ግለሰባዊ ዕቅድ ማቀድ የሚችል ዜጋ መፍጠር እንደሚገባም አሳስበዋል። የእያንዳንዱ ዜጋ ዕቅድ የሀገራዊ ዕድገትንም እንደሚወስን መረዳት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦ ምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየነዳጅ ውጤቶችን ግብይት
Next articleየአፍሪካን የጤና ቴክኖሎጅ ለማሳደግ በኢኖቬሽን መታገዝ ይገባል።