
አዲስ አበባ: ነሐሴ 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ለተፋጠነ ሀገራዊ እድገት እና ለዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በቅንጅት እንሠራለን” በሚል መሪ መልዕክት አራተኛው የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሴክተር መሥሪያ ቤት የጋራ ጉባኤ በቢሾፍቱ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) በ2017 በጀት ዓመት ማኅበራዊ ጥበቃን በየደረጃው በመዘርጋት ልዩ ድጋፍ የሚፈልጉ ዜጎች መብታቸው ተጠብቆ በሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚ እንዲኾኑ ለማስቻል በትኩረት ተሠርቷል ብለዋል።በኢትዮጵያ ለከፋተኛ ችግር የተጋለጡ የማኅበረሰብ ክፍሎችን መታደግ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ኀላፊነት ቢኾንም በዘርፉ ያሉ ችግሮችን በፍጥነት እና በዘላቂነት ለመመለስ የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል ነው ያሉት። “ለዜጎች የጋራ ተጠቃሚነት በቅንጅት መሥራት እንደሚገባም” ገልጸዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባሕል እና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቀሰሙ ማሞ መድረኩ ለሴቶች እና ልዩ ትኩረት ለሚሹ የማኅበረሰብ ክፍሎች ትልቅ ትርጉም ያለው መኾኑን ተናግረዋል።ውይይቱ በዘርፉ የሚስተዋሉ ጉድለቶችን ለመሙላት ተሞክሮዎችን በመለዋወጥ ማኅበራዊ መስተጋብራችንን የምናጠናክርበት ነው ብለዋል።
በ2018 በጀት ዓመት ተተኪዎችን ማፍራት ላይ ያሰብናቸውን እቅዶች ለማሳካት በትጋት ልንሠራ ይገባልም ነው ያሉት።በመድረኩ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የክልል መዋቅር ኀላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት፣ የሴቶች ፌዴሬሽን፣ የአካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን፣ የጡረተኛ አረጋውያን ማኅበር፣ የጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር መሪዎች እና አደረጃጀቶች እየተሳተፉ ነው።
ዘጋቢ፦ ቤተልሔም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!