የሩዝ ምርትን ለማሳደግ ምን እየተሠራ ነው ?

13
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሩዝ በአብዛኛው ሰው የምግብ ገበታ ላይ ከማይጠፉ ምርቶች ውስጥ አንደኛው እየኾነ መጥቷል። ይህ ምርት በኢትዮጵያ ከተዋወቀበት ጊዜ ጀምሮ ተወዳጅነቱ እያደገ ነው ፡፡ነገር ግን ምርቱ ኢትዮጵያ ባላት እምቅ አቅም እና በሚፈለገው ልክ አላደገም። የሩዝ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ በግብርናው ዘርፍ የሚገኙ አካላት በትኩረት እየሠሩ ነው።
ሩዝ ብዙ አርሶ አደሮችን የኑሮ ደረጃን አሻሽሏል። ከምግብ ዋስትና ባሻገር ለገበያ በማቅረብ ገቢያቸውን አሳድገዋል። በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ፣ ደራ እና ሊቦከምከም ወረዳዎች የሚገኙ አርሶአደሮች በሩዝ ምርት የተሻለ ተጠቃሚ ኾነዋል። በደቡብ ጎንደር ዞን በፎገራ ወረዳ የሚኖሩት አርሶ አደር መልኬ መለሰ ሩዝ ቀደም ሲል ከሚያመርቷቸው ሰብሎች የተሻለ ምርት እያስገኘላቸው እንደኾነ ተናግረዋል። በሩዝ ምርት ኑሯቸው እንደተለወጠ ገልጸዋል። አሁን ላይ እስከ ሁለት ሄክታር በሚኾን መሬት ላይ ከ70 እስከ 80 ኩንታል ምርት በማግኘት ጥሪት ማፍራት መቻላቸውን አመላክተዋል።
በደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ የሚኖሩት ሌላኛው አርሶ አደር ዘነበ ማሬ በግብርና ምርምር የተሻሻለ የሩዝ ዝርያ በመጠቀም ምርታቸውን ማሳደጋቸውን ገልጸዋል። በአንድ ሄክታር መሬት ከፍ ያለ ምርት እንደሚጠብቁ የሚናገሩት አርሶ አደሩ ከራሳቸው አልፈው ሠራተኞችን በመቅጠር የሥራ ዕድል መፍጠር እንደቻሉ ተናግረዋል።
የብሔራዊ የሩዝ ምርምር ፕሮግራም አስተባባሪ ሙሉጌታ አጥናፍ (ዶ.ር) የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሩዝ ምርትን ለማሳደግ ሦስት መሠረታዊ ተግባራትን እያከናወነ መኾኑን ተናግረዋል። እነዚህም ቴክኖሎጂን ማፍለቅ፣ ለተጠቃሚዎች ማስተዋወቅ እና መነሻ የሚኾኑ ዝርያዎችን ማባዛት ናቸው።
የአማራ ክልል እንደ ፎገራ፣ ደራ እና ሊቦ ባሉ አካባቢዎች የሩዝ ምርት ለማምረት ሰፊ እምቅ አቅም አለው ብለዋል። ይህንን አቅም በአግባቡ በመጠቀም በሀገር ደረጃ እየተደረገ ያለው የሩዝ ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል ነው ያሉት። በአጭር ጊዜ ውስጥ ከውጭ የሚገባውን ሩዝ በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት የውጭ ምንዛሪን ለመቆጠብ እና ፍላጎትን ለማሟላት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በአማራ ክልል ከደቡብ ጎንደር ዞን በተጨማሪ በሰሜን ጎጃም፣ ምዕራብ ጎጃም፣ አዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምዕራብ ጎንደር እና ማዕከላዊ ጎንደር የሩዝ ምርት በስፋት ሊመረትባቸው የሚችሉ አካባቢዎች ናቸው ብለዋል።ለነዚህ አካባቢዎች ተስማሚ የኾኑ ‘አዝመራ’፣ ‘ፎገራ 1’ እና ‘ሀውልቱ’ የተባሉ የተሻሻሉ የሩዝ ዝርያዎች በምርምር እየተለሙ ለገበሬዎች እየቀረቡ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።
በሄክታር እስከ 60 ኩንታል ምርት ማግኘት እንደሚቻልም አንስተዋል። ይህንን ውጤት ለማምጣትም እንደየ ዝርያው አይነት የተሟላ የምክር አገልግሎት፣ ለአካባቢው የሚመጥን ምርጥ የዘር ዝርያ እና የሰብል እንክብካቤ ፓኬጁን መከተል ወሳኝ ነው ብለዋል። የሩዝ ሰብል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትልቅ ተስፋ እንዳለውም ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ አቅም በመጠቀም የሩዝ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚገባትም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleለመተማ ጠቅላላ ሆስፒታል የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።
Next articleየምሥራቅ ጎጃም ዞን የእንስሳት ተዋፅዖ አቅርቦትን ለማሳደግ እየሠራ ነው።