
ገንዳ ውኃ፡ ነሐሴ 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጎል ኢትዮጵያ የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት መሠረታዊ የሕክምና ቁሳቁስ በምዕራብ ጎንደር ዞን ለመተማ ጠቅላላ ሆስፒታል ድጋፍ አድርጓል። የዞኑ ጤና መምሪያ የሥራ ኀላፊዎች፣ የሆስፒታሉ ተወካይ እና የግብረ ሰናይ ድርጅቱ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት ነው ድጋፉ ርክክብ የተደረገው።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ኀላፊ ጅብሪል መርሻ ጎል ኢትዮጵያ ለመተማ ጠቅላላ ሆስፒታል ላደረገው ድጋፍ ምሥጋና አቅርበዋል።
ድጋፉ የሆስፒታሉን የግብዓት ችግር የሚፈታ መኾኑን ገልጸዋል። ሆስፒታሉ ማኅበረሰቡን በተሻለ መንገድ ለማገልገል በርካታ የሕክምና ቁሳቁስ እንደሚያስፈልጉትም አብራርተዋል።
ይህን በጎ ተግባር በማየት ሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶችም ድጋፍ እንዲያደረጉ ጥሪ አቅርበዋል። የጎል ኢትዮጵያ ድርጅት መተማ ቅርጫፍ ሥራ አሥኪያጅ ተሰማ ረታ (ዶ.ር) ድርጅቱ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው መሠረታዊ የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል። ድርጅቱ ከዚህ ቀደም ለተፈናቃይ እና ለአካባቢው ማኅበረሰብ ድጋፍ ማድረጉንም ጠቁመዋል። ወደፊትም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
በዞኑ ወቅታዊ ተላላፊ ወረርሽኞች ሲከሰቱ ድርጅቱ ናሙናዎችን ወደ አዲስ አበባ በመውሰድ በዞኑ ያለውን የጤና ሥርዓት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። የመተማ ጠቅላላ ሆስፒታል ሜዲካል ዳሬክተር እና የሆሲፒታሉ ተወካይ ሥራ አሥኪያጅ ማንደፍሮ ከፍያለው (ዶ.ር) ድጋፉ የሆስፒታሉን አንገብጋቢ ችግር የሚፈታ መኾኑን ተናግረዋል።መሠረታዊ የሕክምና ቁሳቁሶች አብዛኞቹ ገበያ ላይ የማይገኙ መኾናቸውን ገልጸዋል። አካባቢው ሞቃታማ ስለኾነ የሚከሰቱ ወረርሽኞችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!