
ደሴ፡ ነሐሴ 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ የኮሪደር ልማት ከተማዋን ይበልጥ ውብ፣ ምቹ እና ማራኪ እንዳደረጋት ነዋሪዎች ለአሚኮ ተናግረዋል። በዚህ የኮሪደር ልማት ከ2 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ወገኖች በቋሚ እና በጊዜያዊነት የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል።
የተፈጠረላቸውን የሥራ ዕድል በመጠቀም ራሳቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን እያሥተዳደሩ እንደኾነም በሥራው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ሠራተኞች ገልጸዋል። በደሴ ከተማ አሥተዳደር ከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ምክትል ሥራ አሥኪያጅ እና የኮሪደር ልማቱ አስተባባሪ መንግሥቱ አበበ የኮሪደር ልማቱ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንዲከናወን የኘሮጀክቱ አፈፃፀም በጥብቅ ክትትል እየተመራ ይገኛል ብለዋል።
የደሴ ከተማ ምክትል ከንቲባ ሽመልስ ጌታቸው ልማቱ የዕውቀት ሽግግር የተፈጠረበት እና በጊዜ የለንም መንፈስ በራስ አቅም የተሠራ እንደኾነም አስረድተዋል። በከተማዋ አንድ አውራ መንገድ እንደነበር አውስተው አሁን ላይ አማራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት ማሳለጫ መፈጠሩን ነው ያብራሩት።
ሥራውም ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ መጨረስ እንደሚቻል ትምህርት ተወስዶበታል ነው ያሉት። በዘላቂነት አገልግሎት እንዲሰጥም ተገቢ ጥበቃ እና እንክብካቤ ያስፈልገዋል ብለዋል። ልማቱ የማኅበረሰቡ እና የመንግሥት ቅንጅት ጎልቶ የታየበት እንደኾነ የገለጹት ምክትል ከንቲባው ለዚህም በየደረጃው ያሉ አካላትን አመሥግነዋል።
ዘጋቢ፦ አንተነህ ፀጋዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!