
ከሚሴ፡ ነሐሴ 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የመኸር እርሻ ሥራ በስፋት ከሚከናወንባቸው አካባቢዎች መካከል የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ተጠቃሽ ነው። በብሔረሰብ አሥተዳደሩ አርጡማ ፉርሲ ወረዳ የወገሬ ደበሶ እና የዲምቱ ጨቆርሶ ቀበሌ አርሶ አደሮች አካባቢያቸው ለመኸር እርሻ አመቺ መኾኑን ጠቅሰው ማሽላን በኩታ ገጠም እያለሙ መኾኑን ተናግረዋል።
በመስመር መዝራታቸው የተሻለ ምርት እንዲሰጣቸው የሚያግዝ መኾኑን የጠቀሱት አርሶ አደሮቹ በሄክታር ከ40 ኩንታል በላይ ለማምረት ጠንካራ የሰብል እንክብካቤ እያደረጉ መኾኑን ገልጸዋል። የዲምቱ ጨቆርሶ ቀበሌ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጧሀ አሕመድ በቀበሌው ከ400 ሄክታር በላይ መሬት በክላስተር በማሽላ መሸፈኑን ተናግረዋል። የተሻለ ምርት ለማምረት አረም እና ሌሎች የሰብል ጥበቃ ሥራዎችን አርሶ አደሮች እንዲሠሩ ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
የአርጡማ ፉርሲ ወረዳ ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኪሶ ከፋለ በወረዳው ከ11 ሺህ 600 በላይ ሄክታር መሬት በመኸር ሰብል መሸፈኑን ነው የተናገሩት። የወረዳውን ምርታማነት ለመጨመር አርሶ አደሮች ሙሉ ፓኬጅን ተጠቅመው እንዲሠሩ ጠንካራ ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ ነው ያስገነዘቡት።
የወረዳው አርሶ አደር ለኩታ ገጠም እርሻ ሥራ የሚሰጠው ትኩረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱንም ገልጸዋል። በቂ የግብዓት አቅርቦት እየተደረገ መኾኑንም ተናግረዋል። የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ሀሰን ሰይድ በበኩላቸው በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከ58 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በመኸር ሰብል መሸፈኑን ጠቅሰዋል። ከዚህም ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት ለመሠብሠብ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የተያዘው ዕቅድ እንዲሳካም ለግብዓት አቅርቦት ትኩረት ሰጥቶ በመሠራቱ እስካሁን ከ40 ሺህ በላይ ኩንታል የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ መሰራጨቱን ተናግረዋል። በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በርካታ አካባቢዎች የተፈጥሮ ማዳበሪያ የመጠቀም ልምድ እያደገ መምጣቱንም ነው የገለጹት።ኀላፊው ከ900 ሺህ ኩንታል በላይ መደበኛ ኮምፖስት መቅረቡንም አስረድተዋል።በኹሉም አካባቢ አርሶ አደሮች የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮችን እንዲጠቀሙ መደረጉን ጠቅሰዋል።የብሔረሰብ አሥተዳደሩን ምርት እና ምርታማነት ለማሳደግ ሙሉ ፓኬጅን ተጠቅመው አርሶ አደሮች እንዲሠሩ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!