” ችግር ያልበገራት፤ መገፋት ያላናወጻት”

16

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አንድነት ያጸናት፣ ኅብረት ያቆማት፣ አትንኩኝ ባይነት የጠባቃት ናት። በየዘመናቱ አያሌ ጠላቶች ተነስተውባታል፣ በአራቱም ንፍቅ እየተነሱ ጦር አንስተውበታል፣ በግፍ ዘምተውባታል። እርሷ ግን ሁሉንም ድል አድርጋቸዋለች።

 

ለዘመናት ያጸናችውን ሀገረ መንግሥቷን፣ በደም እና በአጥንት የጠበቀችውን ነጻቷን፣ ያልተበረዘው ማንነቷን፣ የከበረው ታሪኳን ሊያጠለሹባት፣ ነጻነቷን ሊነጥቋት፣ ማንነቷን ሊያጠፉባት ጥረዋል። እርሷ ግን በጠላቶቿ ብዛት ሀገረ መንግሥቷን አላናወጸችም፣ ነጻነቷን አልተነጠቀችም፣ ማንነቷን አሳልፋ አልሰጠችም በልጆቿ አንድነት ሁሉንም ድል መታች፣ በልጆቿ ኅብረት በድል ብቻ ተረማመደች እንጂ።

 

መገፋት አጸናት እንጂ አልጣላትም፣ ችግር አበረታት እንጂ አልሰበራትም። ጠላቶች በበዙባት ጊዜ ትጠነክራለች፣ አንድነቷን ታጸናለች። ኅብረቷን ታደረጃለች። ኢትዮጵያ ሪቂቅ ናት ጠላቶች ድል የማያደርጓት፣ ገፍተው የማይጥሏት። ዘምተው የማይረቷት። ኢትዮጵያ ጽኑ ናት። የጠላት ውሽፍር የማይወዘውዛት፣ ዘመቻ የማይንጣት፣ ድንፋታ የማያሸብራት።

 

ኢትዮጵያ በየዘመናቱ ከሩቅም ከቅርብም የሚነሱ ጠላቶች ነበሯት፣ አሏት፣ ይኖሯታል። ከጠላት ርቃ አታውቅም።

 

ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ “እኛ እና አብዮቱ” በተሰኘው መጽሐፋቸው የኢትዮጵያ ጠላቶች በቅርብ የተፈጠሩ አይደሉም፣ ከጥንት ጀምሮ የነበሩ ናቸው ይላሉ። ከጊዜ ጊዜ፣ ከዘመን ከዘመን ጠላትነታቸው አይለወጥም፣ ጠላትነታቸው ሊለወጥ የሚችለው ኢትዮጵያ ደካማ እና አቅመ ቢስ ኾና ስትበታተን እና ጥቃቅን የጎሳዎች መንግሥት ሲመሰረቱ ብቻ ነው ይላሉ።

 

ተፈጥሯዊ አቀማመጧ፣ የተፈጥሮ ሃብቷ፣ ለየት ብሎ የሚታየው ታሪኳ፣ ድንበሯን እያለፉ የሚሄዱት ትልልቅ ወንዞቿ፣ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ሀብቶቿ ጠላተ ብዙ እንድትኾን አድርገዋታል ነው የሚሉት።

 

በቀይ ባሕር በሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን ይዛ የኖረችው እና በቀይ ባሕር ላይ አያሌ ታሪኮችን የጻፈችው ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር እንዳትጠቀም የሚሹ እና የቀይ ባሕርን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር የሚፈልጉ መንግሥታት ኢትዮጵያ በበጎ ዐይን አይመለከቷትም ነው ያሉት።

 

ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር አቅራቢያ በመገኘቷ የዓለም የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሃብት እና የታሪክ ማዕከል ናት። ይህች በልዩነት የምትታይ እና ከሌሎች የተለየ ታሪክ ያላት ሀገር በቀይ ባሕር አካባቢ ታላቅ ኾና እንድትኖር የማይፈልጉ ብዙዎች ናቸው ነው የሚሉት።

 

በነጻነት፣ በጀግንነት እና በአሸናፊነት የኖረችው ኢትዮጵያ ተዳካማ እና እንደ አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ሃብቷን ክፍት አድርጋ እንድትሰጣቸው የሚፈልጉ ጠላቶች አሏት። ይህን ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚፈልጉ ሁሉ በክፉ ዐይን ያዩዋታል ይላሉ።

 

ዛሬ በሥልጣኔ ገፍተዋል የሚባሉ መንግሥታት ሕዝቦች በዋሻ በሚኖሩበት ዘመን ኢትዮጵያ ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት ታላቅ መንግሥት መሥርታ ሕዝቧን ታስተዳድር ነበር። ኢትዮጵያ መንግሥታዊ ኅልውናዋን በሺህ የሚቆጠር ዓመታት ወደ ኋላ ሄዳ ታሪኳን ስትጠቅስ ‘ዛሬ ታላቅ ነን’ የሚሉ መንግሥታት ይከፋቸዋል።

 

ጥቁር ሕዝብ ይህን ያህል ዘመን ነፃነቱን ጠብቆ መኖሩ ያናድዳቸዋል። ዘመናዊ የጦር መሣሪያ የታጠቀ የነጭ ሠራዊትን ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ምድር ድል መምታታችን ያንገበግባቸዋል። በመኾኑም ይጠሉናል ነው የሚሉት።

 

የረጅም ዘመን ዕድሜ የሌላቸው ሀገሮች እና መንግሥታት ጥንታዊ ሕዝቦችን አጥብቀው ስለሚጠሏቸው ሊያጠፏቸው ወይም ሊያዳክሟቸው ይፈልጋሉ።

 

ብዙ የዓለም ሕዝቦች ሃይማኖት አልባ ኾነው በቆዩበት ዘመን ኢትዮጵያ ሃይማኖትን ተቀብላ በመንፈሳዊ ሥርዓት እና ሕግጋት መተዳደሯ፣ የጥንታዊ የቀናት አቆጣጠር ደንብ እና ሥርዓትን ተከትላ እስከ ዛሬ ቀናትን መቁጠር መቻሏ፣ የራሷ ፊደል ባለቤት መኾኗ፣ ጥንታዊ ሀገር ለመኾኗም ይህንኑ ማረጋገጫ አድርጋ ማቅረቧን አይወዱላትም ይላሉ።

 

ኢትዮጵያ ከሩቅ በመጡት ጠላቶቿ ብቻ ሳይኾን ለዘመናት ጎረቤቶቼ ስትላቸው በኖረቻቸው ሀገራትም በተደጋጋሚ መገፋት እና ክህደት ተፈጽሞባታል። ዛሬም ቢኾን እድገቷን የማይመኙ ጠላቶች ያሏት ሀገር ናት።

 

ከጥንት እስከ ዛሬ ጠላቶቿ እየተደጋገሙ ሲመጡ በአንድነት፣ በጀግንነት እና በኅብረት የመለሱ ኢትዮጵያውያን ዛሬም አንድነታቸውን አደርጅተው ከኖሩ የሩቁንም ኾነ የቅርቡ ጠላት ማሳፈር ይችላሉ። እየቻሉም ነው። እስከዛሬም አጽንቷት የኖረው የልጆቿ አንድነት እና ኅብረት ነው። ኢትዮጵያ ችግሮቿን ተቋቁማ ለአፍሪካውያን ምልክት ናት። ለምሥራቹ አፍሪካ ደግሞ ከፍ ያለ ድርሻ አላት።

 

የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ፕሮፌሰር ቡሩክ ኃይሉ የአፍሪካ ቀንድ አሁንም ያልተረጋጋ ነው ይላሉ፡፡ የኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገራት ከነጻታቸው ማግሥት ጀምሮ ሳይረጋጉ ኖረዋል፡፡ አሁንም ሱዳን እና ሶማሊያ ባልተረጋጋ ሁኔታ ላይ ናቸው ነው የሚሉት፡፡ የጎረቤቶቿ አለመረጋጋት ብቻ አይደለም፣ በጎረቤቶቿ ግጭት እና አለመረጋጋት ታክከው የሚመጡ የኢትዮጵያ ጠላቶች መኖራቸው ነው ችግሩ።

 

በተለይም የሱዳን ጄኔራሎች በፈጠሩት ቁርሾ የተነሳው ጦርነት ሱዳን ባልተረጋጋ ሂደት ውስጥ እንድትቆይ አድርጓታል፡፡ ኢትዮጵያ እንደ መልካም ጎረቤት ለማስታረቅ ብዙ ጥረቶችን ማድረጓንም አንስተዋል፡፡ ኢትዮጵያ የሱዳን ጀኔራሎች ችግሮቻቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ጥረት ከማድረግ ባሻገር ግጭትን ሸሽተው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ በርካታ ሱዳናውያንንም ተቅብላ እያኖረች ነው ይላሉ፡፡

 

ለረጅም ዓመታት በከፍተኛ ያለመረጋጋት ሂደት ውስጥ ያሳለቸፍው ሶማሊያ በችግር ውስጥ መቆየቷን አንስተዋል፡፡ ኢትዮጵያም እንደ ሩቅ ዘመድ ሳይኾን እንደ ቅርብ ጎረቤት ለሶማሊያ ሰላም ትልቅ ሥራ ሠርታለች ይላሉ፡፡ በተለይም በሀገሪቱ አንጻራዊ ሰላም እና መረጋጋት እንዲፈጠር ዋጋ ከፍላለች ነው የሚሉት፡፡

 

ለሶማሊያ ሰላም በአፍሪካ ኅብረት እና ሰላም አስከባሪ ኃይል ወደ ሶማሊያ ሲገባ ኢትዮጵያ ቀዳሚውን ድርሻ ወስዳለች፡፡ ልጆቿን ልካ የሶማሊያን ሰላም ካወኩ ኃይሎች ጋር ተዋግታለች፡፡ የሶማሊያ ሰላም እንዲረጋገጥ ያለ ስስት መስዋዕትነት ከፍላለች ይላሉ።

 

የኢትዮጵያ ሠራዊት በሶማሊያ ላይ ሰላም እንዲመጣ አሁንም መስዋዕትነት እየከፈለ መኾኑን አንስተዋል፡፡ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ለሌሎች እንደምትኖር የሚያሳይ ነው። ኢትዮጵያ እንደ መልካም ጎረቤት ጎረቤቶቿ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍንባቸው ትልቅ ሥራ እንደምትሠራ ነው ያነሱት፡፡ ከጎረቤቶቿ ለኢትዮጵያ ሰላም መታወክ የሚሠሩ ግን እልፍ ናቸው።

 

ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሮቿን፣ በቀጣናው እና ከዚያም አልፎ ያለውን አለመረጋጋት ተቋቁማ በዕቅድ ላይ የተመሠረተ የልማት ሥራዎችን እየሠራች ነው ይላሉ፡፡

 

እርዳታና ምግብ ዋስትና ላይ የተመሠረተ የውጭ ግንኙነት ያለው መንግሥት እና ሕዝብ አደጋ ስላለበት ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ጥሩ ሥራዎችን ሠርታለች ነው የሚሉት፡፡ ይህም ኢትዮጵያ ችግሮች እና ጫናዎች እንደማይበግሯት ማሳያ ነው።

 

ባሕር ኃይልን ጨምሮ ኢትዮጵያ ዘመናዊ ሠራዊትን ገንብታለች፡፡ ሠራዊቱ ደግሞ በሰው ኃይል እና በቴክኖሎጂ የተገነባ ነው የሚሉት ምሁሩ የኢትዮጵያ ቀጣናዊ ተደማጭነት እየጨመረ እና ከፍ እያ መጥቷል ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያ በኢጋድ፣ በአፍሪካ ኅብረት፣ በተባበሩት መንግሥታት ያላት ተሳትፎ እና ተደማጭነት ከፍ ብሏል ነው የሚሉት፡፡ ኢትዮጵያ በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ ከራሷ አልፎ ለአፍሪካውያንም እየሠራች መኾኑን ነው የሚናገሩት፡፡

 

ኢትዮጵያ ሰላምን መሠረት ያደረገ የውጭ ግንኙነት እና የዲፕሎማሲ ሥራዎችን እየሠራች ናት የሚሉት ምሁሩ ችግሮችን በሰላም መፍታት አዋጩ እና ተመራጩ መፍትሔ እንደኾነ ለሩቅም፣ ለቅርብ፣ ለጠላትም ለወዳጅም ሀገራት በግልጽ እየተናገረች ነው ይላሉ፡፡

 

ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ሰላምን ያስቀደመ አካሄድ ትከተላለች። ተንኳሽ እየበዛባትም ለሰላም ታደላለች። ዛሬም ሰላምን አስቀድማ ከጎረቤቶቿ ጋር ትኖራለች። አሁንም የባሕር በር እና ሌሎች ጥቅሞቿን ለማስከበር ሰላማዊ አማራጭን ታስቀድማለች።

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

 

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለሻደይ በዓል የሚመጡ እንግዶች በአግባቡ ለማስተናገድ ዝግጅት ተደርጓል።
Next articleከ58 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመኸር ሰብል መሸፈኑን የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ።