
ሰቆጣ፡ ነሐሴ 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሻደይ በዓል በዋግ ኽምራ ከነሐሴ 16/2017 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 21/2017 ዓ.ም ድረስ በድምቀት የሚከበር የልጃገረዶች የነጻነት በዓል ነው።
የሻደይን በዓል ከመላው የዋግ አካባቢ የተውጣጡ ልጃገረዶች የባሕል ትርዒት ለማቅረብ ወደ ሰቆጣ ከተማ ይገባሉ።
ይህንን የባሕል ትርዒት እና ጨዋታ ለመመልከትም የዋግ ኽምራ ተወላጆች እና ጎብኝዎች ወደ ሰቆጣ ከተማ ያቀናሉ።
የበዓሉን መቅረብ ተከትሎ የሰቆጣ ከተማ ነጋዴዎች እንግዶችን በሚገባ ለማስተናገድ አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል። አሚኮ ያነጋገራቸው በሆቴል ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች እንግዶችን ለመቀበል የቅድመ ዝግጅት ሥራ መሥራታቸውን ገልጸዋል።
ወይዘሮ ቃልኪዳን ቢሰጠኝ በሆቴል ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብት ናቸው። ለሻደይ ባሕላዊ ምግቦችን እና መጠጦችን ባሕሉን በጠበቀ አቀራረብ ለእንግዶች ለማቅረብ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ሻደይ ለዋግ ሕዝብ ባሕላዊ ጨዋታ ብቻ ሳይኾን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ እንደኾነ የጠቆሙት ወይዘሮ ቃልኪዳን ለዚህም ዓመቱን ሙሉ በቂ ዝግጅት እንዳደረጉ ነው የተናገሩት።
የሰቆጣ ከተማ ነጋዴዎች ፕሬዝዳንት አማረ መሰለ የሻደይ በዓልን አስመልክቶ የንግድ ትርዒት እና ባዛር መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
ለንግድ ትርዒት እና ባዛሩ የንግድ እቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ከተለያዩ ከተሞች የተውጣጡ ነጋዴዎች እንደሚሳተፉ ነው ያብራሩት።
በዓሉን ምክንያት በማድረግ የዋጋ ጭማሬ እንዳይኖር ከነጋዴው ማኅበረሰብ ጋር እንደተወያዩ የጠቆሙት አቶ አማረ ሻደይን በዋግ ባሕል እና እንግዳ ተቀባይነት ለማስተናገድ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
በዋግ ኽምራ ያለው አንጻራዊ ሰላም የዘንድሮውን የሻደይ በዓል በድምቀት ለማክበር ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው የገለጹት ደግሞ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ተወካይ እና የዕቅድ ዝግጅት ቡድን መሪ ቢምረው ተስፋየ ናቸው።
የንግዱ ማኅበረሰብ የሚመጡ እንግዶችን በአግባቡ ከማስተናገድ ባሻገር በአልጋ ቤቶች ላይ አስፈላጊውን የጥንቃቄ ሥራ እንዲሠሩ እና ከጸጥታ አካላት ጎን እንዲቆሙም አሳስበዋል።
ያለ አግባብ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይም ሕጋዊ ርምጃ እንደሚወሰድ የገለጹት አቶ ቢምረው ይህንን የሚከታተል ኮሚቴ እንደተዋቀረም ጠቁመዋል።
የሻደይ በዓል በድምቀት ለማክበርም የሰቆጣ ከተማ ቅድመ ዝግጅቷን አጠናቅቃ እንግዶቿን በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች።
ዘጋቢ፦ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!