
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ውኃ ለመያዝ የሚያስችሉ ሥራዎች ከሳምንታት በኋላ እንደሚጠናቀቁ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ገልጸዋል።
በቀጣይ ሳምንታት ቀሪ ተግባራትን በማከናወን ግድቡ የመጀመሪያውን ዙር ውኃ መያዝ እንደሚችል ሚኒስትሩ መግለጻቸውን ኢብኮ ዘግቧል። ይህም በሚቀጥለው ዓመት የቅድመ-ኃይል ማመንጫ ተግባሩን ለማከናወን ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን ነው ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የተናገሩት።
በኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራ ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ልዑክ ዛሬ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን የግንባታ ሂደት መጎብኘቱ ይታዎሳል።
የልዑኩ አባላት ከጉብኝታቸው በኋላ ግድቡ በሚገነባበት አካባቢ ችግኝ መትከላቸውም ታውቋል።