” የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን አንድነት እና ወንድማማችነት የሚረጋገጥበት በዓል ነው” አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር 

21

ባሕር ዳር: ነሐሴ 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በኢትዮጵያ በሁሉም መስክ የማንሰራራት ጉዞ ውጤት እየተመዘገበ ባለበት ወቅት የሚከበር መኾኑ ልዩ እንደሚያደርገው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ተናግረዋል።

 

በፌዴሬሽን ምክር ቤት አሥተባባሪነት እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት ኅዳር 29/2018 ዓ.ም በሆሳዕና ከተማ የሚከበረው 20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን አስመልከቶ የዐቢይ ኮሚቴ ውይይት እየተካሄደ ነው።

 

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን አንድነት እና ወንድማማችነት የሚረጋገጥበት በዓል ነው ብለዋል።

 

የ2018 ዓ.ም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ የማንሰራራት ጉዞን የጀመረችበት እና ውጤትም እየተመዘገበ ባለበት ወቅት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ነው ያሉት።

 

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በሚመረቅበት እና ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ በተደራጀ አግባብ በሚጀመርበት ወቅት መከበሩም ሌላው በዓሉን ልዩ የሚያደርገው እንደኾነ ነው የገለጹት።

 

በዓሉ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እንደሚከበርም ተናግረዋል። በዓሉ የክልሉን የልማት ሥራዎች ለመሠረተ ልማት እና ኢንቨስትመንት መነቃቃት የሚፈጥር ነው ብለዋል።

 

ኢዜአ እንደዘገበው በዓሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ በፌዴራል፣ በክልሎች እና ከተማ አሥተዳደሮች ይከበራል ። የማጠቃለያ መርሐ ግብር ደግሞ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ ይከበራል ነው የተባለው።

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

 

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጾመ ፍልሰታ ሐዋርያት ያጡትን ያገኙበት ሱባዔ” 
Next articleያለበትን ሀገራዊ ኀላፊነት ለመወጣት እየሠራ መኾኑን የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ።