
ባሕር ዳር: ነሐሴ 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጾመ ፍልሰታ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ተናፋቂ አጿማት መካከል አንዷ እንደኾነች ይነገራል። ጾመ ሐዋርያት፣ የሱባዔ ጾም፣ ጾመ ማርያም እየተባለም ይጠራል።
ትርጓሜውን ስንመለከት ፍልሰታ ማለት ፈለሰ፤ ተሰደደ፤ ተጓዘ፤ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሄደ ከሚለው የግዕዝ ግስ የተገኘ ቃል ነው።
ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ “ድንግል ማርያም ከሚያልፈው ዓለም ወደ ማያልፈው ዓለም፣ ከምድር ሕይዎት ወደ ሰማያዊ ሕይዎት ተሻገረች” በማለት ፍልሰታ የሚለውን ቃል በትርጓሜ ገልጾታል፡፡
በዚህ መሠረትም ጾመ ፍልሰታ የቅድስት ድንግል ማርያምን ሥጋዋ ከመቃብር መለየትን እና ወደ ሰማይ ማረግን እንደሚገልጽ የሃይማኖቱ አስተምህሮት ይገለጻል።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዲግሪ የባሕል ጥናት ተማሪ የኾኑት አባ እንድርያስ አምባቸው የፍልሰታ ጾም የቅድስት ድንግል ማርያምን እረፍት እና እርገትን መሠረት ያደረገ እንደኾነ ያስረዳሉ።
አባ እንድርያስ የጾሙን መነሻ ከቅድስት ድንግል ማርያም እረፍት ጋር አያይዘው ሲገልጹ ቅድስት ድንግል ማርያም ያረፈችው በጥር 21 ቀን ነው ይላሉ።
ሐዋርያትም አስከሬኗን ሊቀብሩ ወደ ጌቴሴማኒ ይዘዋት በሄዱ ጊዜ አይሁድ በምቀኝነት እንደተነሱባቸው ያስረዳሉ። በዚህን ጊዜ መላዕክት የድንግል ማርያምን አስከሬን ከአይሁድ ነጥቀው በገነት አኑረውት እንደነበር ተናግረዋል።
ሐዋርያትም አስከሬኑን ፈልገው ያገኙት ዘንድ ከአረፈችበት ስምንተኛው ወር ላይ ከነሐሴ 1 እስከ ነሐሴ14 ሁለት ሱባዔ ገብተው፤ ከጌታችን ተቀብለው በጸሎት እና በምህላ ቀበሯት ይላሉ።
ከተቀበረችም በኋላ በሦስተኛው ቀን አረገች። ትንሳኤዋን ያየ ቶማስ የተባለው ሐዋርያ ብቻ ስለነበር ሌሎች ሐዋርያትም ለድንግል ማርያም ካላቸው ፍቅር የተነሳ ትንሳኤዋን ባለማየታቸው መንፈሳዊ ቅናት እንዳደረባቸው አባ እንድርያስ ገልጸዋል።
በዓመቱም ሐዋርያት ተሰባስበው ቶማስ ትንሣኤዋን አይቶ እኛም በረከት አይቅርብን ብለው ከነሐሴ 1 ጀምረው ለሁለተኛ ጊዜ ሱባዔ እንደገቡ አብራርተዋል።
በዚህን ጊዜ እመቤታችንም ተገለጠችላቸው፤ እያዩዋት አረገች። ጌታችንም የሐዋርያትን ሱባኤ ተቀብሎ እመቤታችንን መንበር፤ ጴጥሮስን ካህን አድርጎ ቀድሶ አቁርቧቸዋል ብለዋል፡፡
ከዚያ ጊዜ በኋላም ሁለቱ የሱባዔ ሳምንታት ጾመ ፍልሰታ ተብሎ ሁሉም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ ይጾመዋል ነው ያሉት፡፡
ጾሙንም ከሥጋ እና ወተት ውጤቶች፣ ሰውነትን ከሚገነቡ ነገሮች በመታቀብ እና በመጾም፣ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሔድ፣ በስግደት፣ በምፅዋት እና በጾሎት እንደሚከናወንም አብራርተዋል።
በጸሎተ ፍልሰታ በቤተ ክርስትያን በ24ቱም ሰዓታት ጸሎት፣ ትምህርት እና ልዩ ልዩ አገልግሎት ይሰጥበታል። ቅዳሴ ማርያም ይቀደሳል፣ ውዳሴ ማርያም ይተረጎማል፣ ሌሎችም መንፈሳዊ ክዋኔዎች ይከወናል ነው ያሉት።
ከምሽት 3:00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋት 11:00 ሰዓት ድረስ ሰዓታት ይቆማል ነው ያሉት። ጠዋት ጀምሮም በነገረ ማርያም፣ በተዓምረ ማርያም ትርጉም እንዲሁም በሥርዓተ ቅዳሴ እስከ 9:00 ሰዓት ድረስ ልዩ ልዩ ሥርዓት እንደሚከናወን አስረድተዋል።
ምዕመናንም ሱባዔ የሚይዙበት፣ ከሐጢዓት በመራቅ ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበት ወቅት እንደኾነም ጠቁመዋል።
ጾመ ፍልሰታ ሰው ራሱን የሚያዳምጥበት፣ የተጣላ የሚታረቅበት፤ ይቅር የሚባባልበት፣ ስለ ሰላም የሚሰበክበት፣ ወደ እግዚአብሔር በመጮህ የምንለምንበት ነው ብለዋል።
ሐዋርያት የጾሙት ያጡትን የድንግል ማርያምን አስከሬን ለማግኘት ነው፤ አግኝተውበታል። እኛም ሰላም አጥተናልና ያጣናውን ሰላም የምናገኝበት የጸሎት ወቅት ነው ብለዋል።
ለስጋም ለነፍስም መልካም ነገርን መሥራት እንደሚገባ አባ እንድርያስ አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን