
አዲስ አበባ: ነሐሴ 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ሰላማችንን ማጽናት ለኢትዮጵያ ማንሰራራት” በሚል መሪ መልዕክት በሰላም ሚኒስቴር አዘጋጅነት በአዳማ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ እንደቀጠለ ነው።
በሰላም ሚኒስቴር የፌዴራሊዝም እና የግጭት አሥተዳደር ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ቸሩጌታ ገነነ ከሚያለያዩ ይልቅ አንድ የሚያደርጉ እና የሚያሰባስቡ ትርክቶችን በማጉላት ሀገራዊ አንድነት እና ሰላምን ማጽናት ይገባል ብለዋል። የሀገራችንን የለውጥ ጉዞ ለማሳካት እና ሰላማችንን እውን ለማድረግ መሪዎች ሰላምን የማጽናት ተግባርን በቁርጠኝነት መሥራት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።
ለሀገር እድገት ቁልፍ ጉዳይ የኾነውን ሰላም ማጽናት እንደ ሀገር የልማት ሥራዎችን በውጤታማነት ለመፈጸም፣ አንድነት እና አብሮነትን ለማጽናት ወሳኝ ጉዳይ እንደኾነ ነው የተናገሩት።
“ሰላም ከሁላችንም መዳፍ የሚገኝ የሁላችንም እኩል ኀላፊነት ነው” ብለዋል። በመግባባት ላይ የተመሠረተ ጽኑ አንድነታችን ማስቀጠል እንደሚገባም ሚኒስቴር ዴኤታው ቸሩጌታ ገነነ ገልጸዋል። የሀገራችንን የለውጥ ጉዞ ለማሳካት እና ሰላማችንን እውን ለማድረግ አመራሩ ሰላምን የማጽናት ሥራን በቁርጠኝነት መተግበር አለበት ነው ያሉት።
ሰላማችንን ሌት ከቀን ልንጠብቀው የሚገባ አንኳር ጉዳይ ነው ያሉት ሚኒስቴር ዴኤታው አንዳችን ለአንዳችን የሰላም ምንጭ እንጂ የግጭት መነሻ እንዳንኾን ከቆረጥን እና ለተግባራዊነቱ ከተጋን እንደ ሀገር ለውጥ ይመጣል ብለዋል። ሰላምን በማጽናት አብሮነት እና አንድነትንም በማጠናከር ኅብረ ብሔራዊነቷ የተረጋገጠ የበለጸገች ኢትዮጵያን መፍጠር እንችላለን ብለዋል። ለዚህ ስኬትም ሁሉም መሪ ሰላም የማጽናት ሥራን ማስቀደም አለበት ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አሰፌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!