
ባሕር ዳር: ነሐሴ 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አበው” ከስብ ስም ይሸታል” ይላሉ በጎ የሠራን ግለሰብ ሲያወድሱ። አንድ ሰው በሕይዎት ሲኖር ከመቃብር በላይ የሚውል ሠናይ ምግባርን አስቀምጦ በማለፍ ስሙን ዘላለማዊ ማድረጉ የሚያስመሰግነው ይኾናል።
ቅን ልቦና ያላቸው ግለሰቦች እና ተቋማትም በዓለም አቀፍ ደረጃ በጎነትን በስፋት በመተግበር ስማቸውን ከማቃብር በላይ ያውላሉ።
በጎነት በዓለም ዙሪያ በስፋት የሚተገበር ነው። ለአስረጅነት የምሥራቅ አፍሪካን ሀገራት እናንሳ። የበጎ ፍቃድ ሥራ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ከሚያበረክትባት ሀገር መካከል ደግሞ ሩዋንዳ በቀዳሚነት ትጠቀሳለች፡፡
የሩዋንዳ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢዋ አኳያ ሲሰላ 30 በመቶውን እንደሚሸፍን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በኬኒያ ደግሞ የበጎ ፍቃድ ሥራ 3 ነጥብ 66 በመቶ አስተዋጽኦ እንዳለው በጥናት ተረጋግጧል።
ወደ ኢትዮጵያ ስንመለስ እስከአሁን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ኢኮኖሚያዊ አስተዋጾኦው ተለክቶ የወጣለት መረጃ ባይኖርም የመስጠት እና የመደጋገፍ ባሕልና እሴትን ከፍ አድርጓል ማለት ግን ይቻላል። ዜጎች ችግሮቻቸውን በጋራ እንዲፈቱም አስችሏቸዋል።
“ነገር በምሳሌ፤ ጠጅ በብርሌ” ያምራል እንዲሉ ኢትዮጵያዊቷ አበበች ጎበና በሺዎች የሚቆጠሩ ወላጅ አልባ ልጆችን አስተምረው ለቁም ነገር በማብቃት በበጎ ምግባራቸው በምሳሌነት ይነሳሉ። ለዚህ መልካም ተግባራቸውም የጅማ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት በመስጠት ዕውቅና ለግሷቸዋል።
ከዚህ አንጻር ዘርፉ በአንድ ማኀበረሰብ ዘንድ ያለን መተሳሰብ በማሳደግ የሰውን ሕይዎት በመታደግ የሕሊና እርካታን ሲያጎናጽፍ ይስተዋላል። ሜቄዶንያ የአረጋውያን እና የአእምሮ ህሙማን ማዕከልም እንድሁ በበጎነት ተግባር የሚታወቅ ትልቅ ተቋም ነው።
በጎ ፍቃደኝነት በቋንቋ፣ በብሔር፣ በሃይማኖት እና በቀለም የሚገደብ ሳይኾን በራስ ተነሳሽነት የሚሠራ ለመኾኑ ደግሞ ማዘር ትሬዛ ⎡እናት ትሬዛ⎤ ያበረከቱት የበጎ ተግባር ተጠቃሽ ናቸው።
እኒህ እናት በጎ ሥራን የሚተገብር ድርጅትን በማቋቋም ከወገናቸው ጎን በመቆም ሕይወታቸውን ሙሉ ድሆችን እና ረዳት የሌላቸውን ዜጎች በማገልገል በዓለም ላይ ሁሉ አዛኝ እናት አስብሏቸዋል፡፡
እንደ ሀገር እና እንደ ክልል እየተተገበሩ ያሉ አሁናዊ የበጎ አድራጎት ሥራዎችም አሉ።
የቅን እጆች ባለቤት እና ምሥጉን የተቋማት መሪዎች በጋ በፀሐይ ሐሩር፣ ክረምት በዶፍ ዝናብ እና ጎርፍ የሚሰቃዩ፣ በውርጭ እና ቁር የሚንገላቱ አቅመ ደካሞችን እየለዩ የቤት ባለቤት በማድረግ ውዳሴ ተችሯቸዋል።
ሕይዎታቸውን ቤዛ ያደረጉ የመጀመሪያ የሕክምና እርዳታ ሰጭ ወጣቶች ደግሞ በበጎ ምግባራቸው በርካታ ነፍስ መታደጋቸው የዓደባባይ ሚስጢር ነው። የተራቆተ አካባቢን ችግኝ በመትከል እና ተንከባክቦ በማጽደቅ በጎ አድራጊዎች እየተጫዎቱት ያለው ሚናም ቀላል የሚባል አይደለም።
ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሲከሰት በጎ አድራጊዎች ከዳር እስከ ዳር ተጠራርተው የአርሶ አደሩን ሰብል ፈጥነው በመሰብሰብ ከጥፋት ሲታደጉ አስተውለናል። ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋ ሲከሰትም እንዲሁ። ጣና ሐይቅን የወረረውን መጤ የእምቦጭ አረም ለማጥፋት የተደረገውን ሀገር አቀፍ ዘርፈ እና ዓይነተ ብዙ ርብርብ ልብ ይሏል።
በየዕለቱ የዜጎች ሕይዎት በትራፊክ አደጋ መቀጠፍ ያሳሰባቸው፣ የሃብት ንብረት ውድመት እንደ እግር ውስጥ እሳት ያቃጠላቸው ባለ ቅን ልቦና በጎ አድራጊዎች ትራፊክ ፖሊሱን በማገዝ ቀላል የማይባል ሕይዎት ከጥፋት አድነዋል፤ ከፍተኛ ሐብት እና ንብረትንም ከውድመት ታድገዋል።
በጎነት አያጎድልም እንዲሉ በክርስቲያን እና ሙስሊም በዓላት ወቅት በጎ አድራጊዎች ለምንዱባን ማዕድ በማጋራት አለኝታነታቸውን አስመስክረዋል። ደም በመለገስ ወገናዊነታቸውን አሳይተዋል። በሌሎችም ሰፋፊ ሰዋዊ አገልግሎቶች ተሳታፊ በመኾን የውዴታ ግዴታቸውን ተወጥተዋል።
አሁን ላይ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተግባር ተቋማዊ እየኾነ መምጣቱም ይበል የሚያሰኝ ነው። “እኮ እንዴት? ” ካላችሁ በየጊዜው በሚፈጠረው የባሕርይ ለውጥ ተቋማት፣ ከከተማ እስከ ገጠር ያሉ ነዋሪዎች፣ ባለ ሀብቶች፣ ወጣቶች እና ሌሎች የበጎ ፍቃድ ማኅበራት በአገልግሎቱ ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተሳትፏቸው እያደገ መጥቷልና ነው፡፡ ይህም አገልግሎቱ ባሕል ወደ መኾን ደረጃ መሸጋገሩን ያመላክታል።
እዚህ ላይ በበጎ አድራጎት የሚከናወኑ ሥራዎች ሁሉ እንከን የለሽ ናቸው ማለቴ ግን አይደለም። በዚህ ዓመት በባሕር ዳር ከተማ አንድ መንግሥታዊ ተቋም በ240 ሺህ ብር ወጭ የአንድን አቅመ ደካማ ቤተሰብ ቤት አፍርሶ በአዲስ ለመሥራት ያስጀምራል።
ከሳምንታት በኋላ ያ ተቋም ቃሉን አክብሮ ቤቱን መሥራቱን ለመታዘብ ወደ ሥፍራው አቀናሁ። በ240 ሺህ ብር ሒሳብ በጣም ትንሽ የእንጨት ቤት ተሠርቶም አገኘሁት። ከልቤ አዘንኩ። “በልጅ አመካኝቶ ይበላሉ አንጉቶ”ን ውስጤ አጫረብኝ። ያን ተግባር የከወኑ አካላት ትዝብት ላይ የወደቁ ናቸው ባይ ነኝ።
ሌላም ማሳያ ልጨምር፤ ባለፈው ዓመት ነው። አንድ ተቋም የአቅመ ደካማ ቤተሰብን ቤት “ልንገነባ ነው” ሲል ማስታወቂያ አስነገረ። ሚዲያዎችም ሥራውን ለመዘገብ በሥፍራው ተኮለኮሉ። ነባሩ ቤትም በደቦ ፈረሰ።
ከወራት በኃላ ያ ተቋም በአዲስ ለመገንባት ብሎ ያፈረሰውን ቤት ሳይጨርሰው ዳናውን አጠፋ። ያካባቢው ነዋሪዎችም ቤቱን እንደነገሩ በመሥራት የአቅመ ደካሞችን ሕይወት መታደጋቸው አይቻለሁ። ይህም የከረመ ትዝብቴ ነው።
“እገሌ የተባለው መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ችግኝ ሊተክሉ ነው” ተብሎ የተወሰኑ መሪዎች ብቻ ወጡ። ታዲያ እንደተባለው ሳይኾን የተወሰኑ ኀላፊዎች ብቻ ለፎቶ ግራፍ ሥነ ሥርዓት “ችግኝ ሲተክሉ የሚያሳብቅ ፎቶ ተነስተው በማኅበራዊ ሚዲያ አጋሩ። ይህስ እስከ መቸ መቀጠል አለበት ትላላችሁ አንባቢያን?
በግሌ በመምሰል ያደገ ግለሰብ፣ ኅብረተሰብ እና ሀገር የለምና ራስን መኾን ይበጃል እላለሁ። በርካታ በጎ ተግባራት ያሉን ቢኾንም እንኳ የይምሰል በጎነቶች ግን ቢቀሩ ከሚሉት ውስጥ ነኝ።
ዘጋቢ፦ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን