“ድሬዳዋ በታሪክ ገጽ”

19

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ድሬዎች በታሪክ አጋጣሚ በዚህ ሳምን ነሐሴ/1998 ዓ.ም መዝናናት ያሰቡት እየተዝናኑ፤ የሚሠሩት የዕለት ሥራቸውን ከውነው እረፍት ለማድረግ ወደ መኝታቸው ባመሩበት ወቅት ነበር አንድን የታሪክ ምዕራፍ ያስተናገዱት።

ሀገር ሰላም ብለው በተኙበት የውድቅት ለሊት ግን ያላሰቡት እና የማይወዱት ጭንቅ ጣለባቸው። ከባድ ዝናብ ጥሎ ድሬ በጎርፍ ተመታች።

ድሬ ቀድማ የጎርፍ መከላከያ አልሠራችም እና የሰማዩን ቁጣ መቋቋም አቃታት። በዚህም ብዙዎች ለጉዳት ተዳረጉ። ቤተሰብ ተለያየ። ሀዘን በድሬዎች ቤት ገባ። ይሄኔ ታዲያ መላው ኢትዮጵያውያን አብረው አዘኑ።

ጉዳት ለደረሰባቸው ስድስት የከተማ እና ሦስት የገጠር ቀበሌዎችን ለማገዝ ሁሉም በአንድ ልብ ተነሳ። ይህ አደጋ ከባድ እና አሳዛኝ ቢኾንም የኢትዮጵያን የመረዳዳት እና የመተባበርን ባሕል በግልጽ ያሳየ ክስተት ኾኖ አለፈ።

መንግሥታዊ ተቋማት፣ ግለሰቦች እና በጎ አድራጊዎች ሁሉ ለተጎጂዎች ለመድረስ ተረባርበዋል። በወቅቱ የነበሩት የመንግሥት ኀላፊዎች የደረሰውን ጉዳት በቦታው ተገኝተው የተመለከቱ ሲኾን መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተው ተግብረዋል፤ አጽናንተዋል። ለተጎጅዎች የገንዘብ እርዳታ ለማሠባሠብ በተከፈተው የባንክ ሂሳብ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ አድርገው ከጎናቸው እንዳሉ አሳይተዋል።

ከአደጋው በኋላ የድሬዳዋ ከተማ አሥተዳደር እንደዚህ ዓይነት አደጋ ዳግም እንዳይከሰት ለመከላከል ዘላቂ መፍትሔዎችን መተግበር ላይም መሥራት መጀመሩን ታሪክ ያስታውሰናል። በየዓመቱ የችግኝ ተከላ ዘመቻ በማካሄድ እና የአካባቢውን ደን በማልማት የጎርፍ አደጋን ለመቀነስም ሥራዎችን ሠርቷል።

ይህ አሳዛኝ ታሪክ የድሬዳዋን ነዋሪዎች እና መላው ኢትዮጵያውያንን አንድ በማድረግ የመከራ ጊዜን በጋራ እንዴት መወጣት እንደሚቻል አሳይቷል። ወቅቱ የክረምት ወቅት ነውና ዛሬስ እንደዚህ አይነት አሳዛኝ ክስተቶች እንዳይከሰቱ ምን አይነት ጥንቃቄ እያደረግን ይኾን ምንጭ፦ አዲስ ዘመን ጋዜጣ

✍️ “የ13 ወር ጸጋ”

የነሐሴ ወር የመጀመሪያው ሳምንት ላይ እንገኛለን። የነሐሴ ወር በኢትዮጵያ ታሪካዊ ብቻ ሳይኾን ተፈጥሯዊ ክስተቶች የሚበዙበትም ነው። ብዙ የባሕል እና ቱሪዝም ሁነቶች የሚከናወኑበት ወቅትም ነው። ወዲህ ደግሞ የአዲስ ዘመን መቀበያ እና መንደርደሪያ ተደርጎ ይወሰዳል።

የተሰናባች ዓመትን እየተሰናበቱ የአዲሱን ዓመትን እየናፈቁ የሚቆዩበት ልዩ ወር ነው። በዚህ ወር ውስጥ ባሕላዊ እና ተፈጥሯዊ ሁነቶች ይበዛሉ። ይህ ወር ሲያልቅ የሚያስከትለው የአጭሯ ቀናት የ13ኛ ወር ልዩ ጸጋ ተደርጋ ትወሰዳለች። ይህችን ወር ታዲያ ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን ለማስተዋወቅ ተጠቅመውባታል።

በዚህ ሳምንት ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ የቀረበው የ13 ወር ጸጋ (Thirteen Months of Sunshine) የሚለው የእንግሊዘኛ ቃል ኢትዮጵያን ለዓለም አስተዋውቋል።

የእንግሊዘኛ ፕሮግራሞች ማስጀመሪያ እንዲኾን ተደርጎም አገልግሏል።

ይህ ቃል ለ50 ዓመታት ያህል የኢትዮጵያ የቱሪዝም ማስታወቂያ መሪ ቃል ኾኖ አገልግሏል። አሁን “ምድረ ቀደምት” በሚል ቢተካም ኢትዮጵያን ለዓለም አስተዋውቋል እና እነሆ ታሪክ ሲዘክረው ይኖራል።

የዚህ መሪ ቃል ፈጣሪ እና “የቱሪዝም አባት” በመባል የሚታወቁት ሀብተሥላሴ ታፈሰ ናቸው። ምንጭ፦ አዲስ ዘመን ጋዜጣ

✍️ “የአሩሻ የሰላም ስምምነት”

በ1990 መገባደጃ ላይ በጥቁር ደመና የተጋረዱት ሩዋንዳውያን አንዱ በሌላው ወንድሙ ላይ የዘር ልዩነት በመፍጠር ተጋድለዋል። ሀገርንም ወደ ኋላ ጎትተዋል። የዛሬን አያድርገውና ሩዋንዳውያን ዓለም ለእርስ በእርስ መጫረስ እንደ ምሳሌ አድርጎ ሲቆጥራቸው ቆይቷል። ይህን አስከፊ ጊዜ ሩዋንዳውያን ሲያስታውሱት ይቆጩበታል። ወገናቸውን በዕውቀት ማጣት አጥተዋልና።

የጦርነቱ ዋና ምክንያት የጎሳ ግጭቶች ሲኾኑ በተለይም በሁቱ እና ቱትሲ ማኅበረሰቦች መካከል የነበረው የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ውጥረት እንደኾነ ይታመናል። አር ፒ ኤፍ (RPF)፣ በዩጋንዳ የስደተኞች ካምፖች ውስጥ የተመሠረተ የቱትሲ ታጣቂ ቡድን ሲኾን ወደ ሩዋንዳ በመግባት በሀገሪቱ የእርስ በእርስ ጦርነት ተሳትፎ አድርጓል።

ይህ ጦርነት የሩዋንዳን ሕዝብ እና ኢኮኖሚ በእጅጉ ሲጎዳ ቆይቷል። ጦርነቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተለያዩ ሙከራዎች ቢደረጉም ዘላቂ መፍትሔ ላይ መድረስ አልተቻለም። በዚህ ወቅት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እና የአፍሪካ ታላላቅ ሀገራት መሪዎች የሩዋንዳን ችግር በውይይት እንዲፈታ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ጀመሩ።

በመጨረሻም ረጅም ጊዜ የፈጀው ድርድር እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር በ1993 በዚህ በያዝነው ሳምንት ተጠናቀቀ። የሩዋንዳ መንግሥት እና አር ፒ ኤፍ አምስት የተለያዩ ፕሮቶኮሎችን የያዘውን “የአሩሻ የሰላም ስምምነትን” ፈረሙ። ይህ ስምምነት በሩዋንዳ ውስጥ የሰላም፣ የዴሞክራሲ እና የብሔራዊ እርቅን ለመገንባት ያለመ ነበር።

የአሩሻ ስምምነት በሩዋንዳ ውስጥ ለሰላም መረጋጋት እና ዴሞክራሲ እጅግ አስፈላጊ እርምጃ ነበር። ምንጭ፦ አፍሪካን ሴንተር ፎር ስትራቴጅካል ስተዲ።

ዘጋቢ: ምሥጋናው ብርሃኔ

አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሰላም አማራጭን የተቀበሉ ታጣቂዎች አቀባበል ተደረገላቸው። 
Next article“ህያው አሻራዎች”