
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ለበርካታ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ ዳርጓል። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሕጻናት ከትምህርት ገበታቸው አስተጓጉሏል፤ ለሥነ ልቦና ጫናም ዳርጓል። ዜጎችንም በሰላም ወጥተው ለመግባት፣ ሠርተው ለመኖር አስቸጋሪ አድርጎባቸው ቆይቷል። ሰላምን ላማምጣት በሚደረገው ጥረት አማኙን በመምከር፣ በመገሰጽ እና በማስተማር በኩል የሃይማኖት ተቋማት እና መሪዎች ከፍተኛ ሚና አላቸው።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ መልዓከ ብርሃን ፍስሀ ጥላሁን ሰላም ከጠፋ በምድር ላይ ያሉ ፍጥረታት ሁሉ ይጠፋሉ ብለዋል። የሰው ልጅም አጊጦ እና አምሮበት እንዲኖር መሠረቱ ሰላም መኾኑን ነው የተናገሩት። በቤተክርስትያንም ዓመቱን ሙሉ ስለ ሰላም ይጸለያል ነው ያሉት።
የሰላምን ዋጋ ጠንቅቆ ካለመረዳት የተነሳ የሰላም እጦት እየገጠመ እንደኾነም አስረድተዋል። በየሃይማኖት ተቋማት የሚሰጠውን ትምህርት መከተል እና የአባቶችን ድምጽ ማድመጥ እንደሚገባ ገልጸዋል።”ወንድሞች በአንድ ላይ ኾነው ቢመክሩ መልካም ነው” እንደተባለው ሰዎች በጋራ መክረው ተደማምጠው የሃሳብ የበላይነትን ቢያከብሩ ግጭት አይፈጠርም፤ ሰላማችንም አይደፈርስም ብለዋል።
ማስተማር እና ማስታረቅ የሃይማኖት አባቶች መሠረታዊ ተግባራት መኾናቸውንም አንስተዋል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንም ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ እስከታች ድረስ የሚያሸማግል እና የሚያስታርቅ የሽምግልና ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሠራ እንደኾነም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ጀውሐር መሐመድ ሰላም የሚጀምረው ከራስ ነው ብለዋል። ሰላም ለፈጣሪ ከሚታመን ሰው ሁሉ የሚጠበቅ ነው ብለዋል። ።
ፈጣሪ የሰጠን ሀገር ሰላም እንድትኾን ፈጣሪን በመፍራት ሰላማዊ መኾን ያስፈልጋል ነው ያሉት። የሰላም እጦት ምክንያት የሚኾነውን የፍትሐዊነት መጓደልን ማስተካከል እንደሚገባም አመላክተዋል። ከፈጣሪ መውጣታችን ደም እየፈሰሰ፣ ሰው እየተሰረቀ እና እየታገተ ዝም እንድንል አድርጎናል የሚሉት ፕሬዝዳንቱ ወንጀል መብዛቱን እና ኃጢአት መበርከቱን ነው የተናገሩት። ይህ ደግሞ ለአላህ አለመገዛትን ነው የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በሁሉም መስጊዶች ስለ ሰላም ይሰበካል ያሉት ሼህ ጀውሃር የሰላም እና የእርቅ ግልግል የሚል ዘርፍ በማቋቋም የተጣላን በማስታረቅ ሰላም እንዲመጣ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል። በኢትዮጵያ ወንጌላውያን ኅብረት የባሕር ዳር ከተማ ዋና ጸሐፊ መጋቢ ደሳለኝ አባተ ሰላም ከፈጣሪ የተሰጠ፤ የሰው ልጆች ሁሉ ሊጠብቁት የሚገባ ግምት የሌለው ሃብት ነው ይላሉ። ይህንን የፈጣሪን ስጦታ መጠበቅ እንደሚገባም አንስተዋል።
የእኔ ሃሳብ ብቻ ይደመጥ የሚል አስተሳሰብ ወደ ግጭት እንደሚወስድም ጠቁመዋል። የሃሳብ ግጭት ሕያው ነው፣ ነገር ግን በሃሳብ ማሸነፍን ብቻ ሳይኾን የአሸናፊውን ሀሳብ መቀበልም ያስፈልጋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን የባሕር ዳር እና ደሴ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አባ ስንታየሁ ገላው ሰላም አማራጭ የሌለው የጋራ እሴታችን እና ሃብታችን ነው ብለዋል። የሰላም አለቃ በኾነው በኢየሱስ ክርስቶስ አምሳል የተፈጠረው ሰው ቃሉን በመፈጸም ሰላምን መጠበቅ የግዴታ መኾኑን አስረድተዋል። ወደ ፈጣሪ በመመለስም ሰላምን መፍጠር ይገባል ነው ያሉት።
መንግሥት የሚነሱ ጥያቄዎችን በመለየት ቶሎ ቶሎ ምላሽ መሥጠት እንደሚገባውም አመላክተዋል። በመንግሥትም ይሁን በሃይማኖት አባቶች የሚተላለፉት መልዕክቶች ከስሜት የጸዱ መኾን እንደሚገባቸውም የሃይማኖት አባቶች አሳስበዋል። በየሃይማኖት ተቋማቱ ያሉ የሃይማኖት መሪዎች አርዓያ በመኾን አማኙን ማስተማር እንደሚገባቸው አመላክተዋል። ኀብረተሰቡም አባቶችን በመሥማት እና በማክበር ወደ ፈጣሪ መመለስ እንዳለበት አስገንዝበዋል። ከግጭት የሚገኝ ትርፍ፣ በጦርነት የሚመለስ ጥያቄ አለመኖሩን በመገንዘብ መደማመጥ እና በሰላም መነጋገርን መምረጥ እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች መክረዋል።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!