በበጀት ዓመቱ ከ707 ሺህ በላይ የምዝገባ አገልግሎት መስጠቱን የአማራ ክልል ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎት አስታወቀ።

28
ባሕር ዳር: ነሐሴ 3/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎት ከሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን መሪዎች እና ባለሙያዎች ጋር ተወያይቷል። የውይይቱ ተሳታፊዎች የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎት መረጃ የሚሰነድበት ወሳኝ ተቋም መኾኑን ገልጸዋል።
ተቋሙ በጸጥታ ችግር ውስጥም ኾኖ የሚበረታታ ሥራ መሥራቱን ተናግረዋል። ዲጂታላይዜሽን እንዲስፋፋ እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ መሥራቱንም አንስተዋል።
የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎቱን ከሌሎች ተቋማት ጋር አቀናጅቶ መሥራት፣ አፈጻጸምን ማሻሻል እና ግንዛቤን ማሳደግ እንደሚገባም ገልጸዋል። በተለይም በትምህርት ቤቶች እና በጤና ተቋማት ግንዛቤ በመፍጠር የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አገልግሎቱን ከፍ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። በአርዓያነት የሚጠቀሱ የምዝገባ ጣብያዎችን መፍጠር እና ማዘመን ይገባል ብለዋል።
የሃሰተኛ ማስረጃዎችን ለመከላከል በጋራ መሥራት እንደሚገባም አንስተዋል። ሃሰተኛ ማስረጃዎችን የሚያዘጋጁ እና የሚጠቀሙ አካላት መኖራቸውንም ገልጸዋል። ከሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን ጋር ያለውን ጥብቅ ግንኙነት አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም አመላክተዋል። የአማራ ክልል ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎት ኀላፊ መዓዛ በዛብህ ተቋማቸው ከበርካታ ተቋማት ጋር ግንኙነት እንዳለው ገልጸዋል። በ2017 በጀት ዓመት የመዝገብ አገልግሎት ለማሳለጥ፣ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት መሥራታቸውን ገልጸዋል።
ምዝገባውን በቴክኖሎጂ ለማካሄድ መሠራቱን የተናገሩት ኀላፊዋ በዓመቱ ከ707 ሺህ በላይ ዜጎችን መመዝገባቸውን ተናግረዋል። ይህም ትልቅ ሥራ መኾኑን ገልጸዋል። በስድስት ሪጂዮፖሊታንት ከተሞች በ171 የምዝገባ ጣቢያዎች በቴክኖሎጂ እየመዘገቡ መኾናቸውን ተናግረዋል። ይህም በችግር ውስጥ ኾኖ የተሠራ ትልቅ አፈጻጸም መኾኑን ገልጸዋል። በቴክኖሎጂ በመመዝገባቸው የዜጎችን ድካም እና እንግልት መቀነሳቸውን፣ ፈጣን አገልግሎት መስጠታቸውን፣ በወረቀት ሲሰጥ የነበረውን የቆዬ አሠራር ማስተካከላቸውን ተናግረዋል። ይወጡ የነበሩ ወጪዎችን ማስቀረታቸውንም ገልጸዋል።
የሲስተም መቆራረጥ እንዳይኖር እና ደኅንነቱ የተጠበቀ እንዲኾን በትኩረት መሠራቱንም ተናግረዋል። ዲጅታላይዜሽንን የማስፋት ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተመላክቷል።በ405 ሆስፒታል እና ጤና ጣብያዎች ላይ ምዝገባ መጀመራቸውን የተናገሩት ኀላፊዋ ይህም ከተቋማት ጋር ያላቸውን ጥብቅ ግንኙነት የሚያሳይ መኾኑን ገልጸዋል። ይህ አሠራር ለምዝገባ ሥርዓቱ ውጤታማነት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አንስተዋል።
የመልካም አሥተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል። የወሳኝ አገልግሎት ምዝገባ እንዳይስተጓጎል ማድረጋቸውንም ተናግረዋል። በመጠለያ ጣብያዎች ላይም የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እንዲደረግ ተደርጓል ነው ያሉት። ለተሠራው ውጤታማ ሥራ የሚዲያ አካላት አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበር አንስተዋል። የሃሰተኛ መረጃ መበራከት ለሥራቸው ፈታኝ እንደኾንም ገልጸዋል። የሃሰተኛ ማስረጃዎችን ለመከላከል ከፍትሕ እና በፖሊስ ተቋማት ጋር እየሠሩ መኾናቸውን አመላክተዋል።
በክልሉ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር እንደ ምክንያት በመጠቀም ሃሰተኛ ማስረጃዎችን የሚያመጡ አካላት መበራከታቸውን ገልጸዋል። የሃሰተኛ ማስጀራቸውን ለመከላከል የሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን አካላት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጠይቀዋል። የግንዛቤ ፈጠራ ሥራው አሁንም በሚጠበቀው ልክ ባለመኾኑ ኅብረተሰቡ በጊዜው የወሳኝ ኩነት አገልግሎት እንደማይፈጽም ተናግረዋል። የተቋማት ቅንጅት ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውም አመላክተዋል። የክልሉን ሕዝብ መረጃ በተገቢው መንገድ ለመያዝ የሁሉንም ትብብር እና ቅንጅት እንደሚጠይቅ አንስተዋል።
የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) የአማራ ክልል ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎት በ2017 በጀት ዓመት የተሻለ ሥራ መሥራቱን ገልጸዋል። አገልግሎቱ መረጃ ላይ መሠረት ያደረገ የትውልድ ግንባታ ሥራ እንደሚሠራ ተናግረዋል። ተቋማት የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎትን መደገፍ እንደሚገባቸው አመላክተዋል።
መረጃ ለሀገር ዕድገት እና ሥልጣኔ ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል። መረጃን ለማኅበረሰቡ በማድረስ የወሳኝ ኩነት አገልግሎትን ሥራ ማፋጠን እንደሚገባ ተናግረዋል። የሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን መዋቅሩ መልካም ነገሮችን ለማስረጽ እና አፍራሽ ተግባራትን ለመመከት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አንስተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleሴቶች በማኅበራዊ እና በፖለቲካው ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደግ ይገባል።
Next articleሰላም አማራጭ የሌለው የጋራ ዕሴት እና ሃብት ነው።