
ደሴ፡ ነሐሴ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደሴ ከተማ ሴት ነዋሪዎች ጋር የመራጭ ተመራጭ ሕዝባዊ ውይይት ተካሂዷል። ውይይቱን የመሩት የደሴ ከተማ ሕዝብን ወክለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የኾኑት ማህተመ ኀይሌ (ዶ.ር) ናቸው። በውይይቱ የተሳተፉ ነዋሪዎች ተመራጯ በተለያዩ ጊዜያት ኅብረተሰቡን በማወያየት የሕዝብ ድምጽ ለመኾን እያደረጉት ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው ብለዋል ።
የደሴ ከተማ የፍሳሽ ማስወገድ ሥርዓት፣ የንፁሕ መጠጥ ውኃ ችግር፣ የደሴ ኮምቦልቻ ዋሻ መንገድ፣ የአዲስ አበባ ደሴ ፈጣን መንገድ እና የደሴ ከተማ የመሬት መንሸራተት አሁንም ምላሽ የሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎች መኾናቸውን የውይይቱ ተሳታፊዎች አንስተዋል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ማህተመ ኀይሌ (ዶ.ር) ባለፉት አራት ዓመታት ከ5ሺህ በላይ የማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል።
አሁን ላይ ሴቶችን በተለየ መልኩ ለማግኘት የተፈለገው በማኅበራዊ እና በፖለቲካው ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ እንደኾነም ነው ያስረዱት።የደሴ ኮምቦልቻ የዋሻ መንገድ እና የአዲስ አበባ ደሴ ፈጣን መንገድ ግንባታ ጥያቄዎች ለሚመለከተው አካል ቀርበው በዕቅድ ደረጃ መያዛቸውን ጠቁመዋል።በቀጣይም የተነሱ የኅብረተሰቡን ጥያቄዎች ለሚመለከተው አካል በማቅረብ ምላሽ እንዲያገኙ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- አበሻ አንለይ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን