
አዲስ አበባ: ነሐሴ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰላም ሚኒስቴር” ሰላማችን ማጽናት ለኢትዮጵያ ማንሠራራት” በሚል መሪ መልዕክት ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።ሰላም ለአንድ ሀገር እድገት ቁልፍ ጉዳይ ነው። የሀገር ልማት፣ አንድነት እና አብሮነትን ለማጽናት ሰላምን መጠበቅ እና ማጽናት ሲቻል እንደኾነ የተናገሩት የሰላም ሚኒስትሩ ሙሐመድ እድሪስ ናቸው።
በማንኛውም ሁኔታ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በቁርጠኝነት እና በራስ ተነሳሽነት በመፍታት ሰላምን የማጽናት ብቃትን ለማሳደግ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑንም ሚኒስትሩ አንስተዋል።የሰላም ሚኒስቴር እንደ ሀገር በማኅበረሰቡ መካከል የመቀራረብ፣ የመነጋገር እና በሠለጠነ እና በተቀናጀ መንገድም የአካባቢን ሰላም በመጠበቅ የተቀናጁ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደኾነ ተናግረዋል። እንደ ሀገር ሰላምን በማጽናት ለልማት ሥራዎች ምቹ ሁኔታን መፍጠር ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የመቻቻል እና የመተማመን ባሕልን ማዳበር እና “ሰላም እና ልማትን የሚያውኩ ፀረ ልማት አካሄዶችን የመከላከል አቅምን በማሳደግ ረገድ በርካታ ተግባራት መሠራታቸውንም” ጠቁመዋል። በቀጣይ እንደ ሀገር በሰላም እና በልማት መካከል ያለውን ግንዛቤ ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል። መሠረታዊ የኾኑ የግጭት መከላከያ እና የግጭት አፈታት ሥርዓቶችን ማጎልበት ተገቢ እንደኾነም ነው የገለጹት።
በጋራ በመሥራት ሀገራዊ ሰላምን፣ አብሮነትን እና የጋራ እድገትን መገንባት ያስፈልጋል ነው ያሉት። በሰላም ውይይቱ ላይ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር መላኩ ፋንታ፣ የሰላም ሚኒስቴር ከፍተኛ መሪዎች፣ የሁሉም ክልሎች እና ከተማ አሥተዳደሮች የሰላም እና ጸጥታ ዘርፍ ኀላፊዎች እየተሳተፉ ነው።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አሰፌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን