
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ባለሥልጣን የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸሙን እየገመገመ ነው። የአማራ ክልል ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ባለሥልጣን ኀላፊ ዘውዱ ማለደ በበጀት ዓመቱ የትኩረት መሥኮች ተለይተው በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።
የመፈጸም እና የማስፈጸም አቅምን ለመገንባት በቴክኖሎጅ የታገዘ ሥራ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል። የአሽከርካሪ እና ተሽከርካሪ ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ቴክኖሎጅን መሠረት ባደረገ ሲስተም ለመሥራት ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል። ለአብነትም ሕገ ወጥ መንጃ ፈቃድን በሲስተም የመለየት፣ የስመ ንብረት ዝውውር፣ የተሽከርካሪ ግመታ እና ሌሎችንም ሥራዎች ከእጅ ንኪኪ ነጻ በኾነ የቴክኖሎጅ አሠራር የተተገበሩ መኾናቸውን አንስተዋል።
ከ490 ሺህ በላይ የተሽከርካሪ መረጃዎች በቴክኖሎጅ በተደራጀ መልኩ መያዛቸውንም አብራርተዋል። ከ140 ሺህ በላይ የአሽከርካሪዎች መረጃም በቴክኖሎጅ መያዙን ገልጸዋል።መናኾሪያዎች፣ ፓርኪንጎች፣ የትራፊክ ኮምፕሌክስ እና ሌሎችንም የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶች እንደተሠሩም ተናግረዋል።በመናኾሪያዎች ዘመናዊ የአገልግሎት አሰጣጥን ለመስጠትም በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን አመላክተዋል።
በትክክል ተፈትኖ ያለፈ እና ብቃት ያለው አሽከርካሪን ለመፍጠር በቴክኖሎጅ የተደገፈ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም አብራርተዋል። ይህንን ለማሳካትም በክልል ደረጃ ሲስተም አስለምቶ በመጠቀም በቀጥታ ክትትል እና ቁጥጥር ማድረግ መቻሉንም አንስተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ እና የሰሜን ሸዋ ዞን ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ደጀኔ በቀለ በበጀት ዓመቱ አገልግሎት የሚሰጡ መናኾሪያዎችን ምቹ የማድረግ ሥራዎች ማከናወናቸውን ተናግረዋል። በዞኑ በስድስት መናኾሪያዎች የኢ- ትኬቲንግ አገልግሎት በማስጀመር የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ጥረት ተደርጓል ነው ያሉት።
ቀልጣፋ እና ውጤታማ አሠራርን ለማረጋገጥ ከአጋር እና ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። የደቡብ ወሎ ዞን ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ከድር ይመር በባለሥልጣኑ እየተተገበረ የሚገኘው የዲጂታላይዜሽን አሠራር የሕዝብን እንግልት የሚቀንስ እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን የሚፈታ መኾኑን አንስተዋል። ግልጽ እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዝም ነው የገለጹት።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን